ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የጸጥታው ምክር ቤት ዛሬ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ጉዳይ በዝግ እንደሚመክር ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20/2016 ዓ.ም፡- ከኢትዮጵያ በኩል ተቃውሞ ቢቀርብበትም የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ጉዳይ ዛሬ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም በዝግ እንደሚመክር ተጠቆመ።

“ሰላም እና ጸጥታ በአፍሪካ” በሚል ርዕስ በዛሬው ዕለት የሚሰበሰበው የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ስለተፈጠረው ውጥረት ይመክራል ተብሏል።

ሶማሊያ ለጸጥታው ምክር ቤት ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም የጻፈችውን ደብዳቤ ተከትሎ የወሩ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት የሆነችው ፈረንሳይ ምክክሩን ማሰናዳቷ ተጠቁሟል።

ሶማሊያ ለምክር ቤቱ በጻፈችው ደብዳቤ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ የሶማሊያን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት በጣሰ መልኩ የተከናወነ ነው ስትል ሶማሊላንድን የግዛታ አካሏ በማድረግ መከራከሪያ አቅርባለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ለምክር ቤቱ በጻፈችው የምላሽ ደብዳቤ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ለመወያየት ዝግጁ መሆኗን በመግለጽ እና ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክርቤት የታየ በመሆኑ የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ዙሪያ መምከር እንደሌለበት አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ በደብዳቤዋ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ አለምአቀፍ አሰራርን በተከተለ አኳኋን እንዲሁም የጋራ ተቀባይነት ባገኘ የንግድ መንገድ የባህር በር እንድታገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልጻለች።

ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት በሚያካሂደው ምክክር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ሀና ስርዌ ቴተ ቀርበው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ተጠቁሟል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button