ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በከባድ ማሳሪያ የታገዘ ግጭት ያስተናገደችው ባህርዳር ወደ መደበኛ እንቀስቃሴ ተመለሰች

አዲስ አበባ የካቲት 25/ 2016 ዓ/ም፦ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ባሳለፍነው ሳምንት ሃሙስ የካቲት 21/ 2016 ዓ/ም ግጭት የተካሄደባት የአማራ ክልል መዲና ባህርዳር ወደ መደበኛ (ሰላማዊ) እንቀሰቃሴ መመለሷን ነዋሪዎች ገለጹ። 

በከተማዋ “አባይ ማዶ” እና “ቀበሌ 14” እንዲሁም ዳያስፖራ ሰፈር ባሳለፍነው ሃሙስ ምስት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በከባድ መሳሪያ ታግዞ የተካሄደ ነበር። 

ቅዳሜ ጠዋት ድረስ የተኩስ ልውውጦች መቀጠላቸውን የጠቀሱት አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የባህር ዳር ነዋሪዎች ከሰዓት በኋላ ግን ሁኔታው መሻሻሉን ገልጸዋል። 

ግጭቱን ተከትሎ አባይ ማዶ በሚባል አካባቢ የመንግስት እና የፋኖ ታጣቂዎች አስክሬን መንገድ ላይ ማየታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ በከተማዋ መረጋጋት መታየቱን እና የትራንስፖርት እና የባንክ አገልግሎት እንዲሁም ሊሎች አገልግሎቶች ቅዳሜ ዕለት መጀመራቸውን አክለው ገልጸዋል። 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ትምህርት መጀመሩን እና የተቋሙ ሰራተኞች ወደ ስራቸው መመለሳቸውን ገለጿል። 

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ትላንት ባወጣው መግለጫ “በባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሷል” ሲል ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የከተማ አሥተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው፤ የካቲት 22/2016 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ የጸጥታ ችግር ገጥሞ እንደነበር ተናግረዋል።  የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ  የጸጥታ ተቋማት ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በወሰዱት ሕግ የማስከበር ተግባር “ኀላፊነት የጎደላቸው አካላት” በከተማዋ እና በነዋሪዎች ላይ ያቀዱት ትርምስ ሳይሳካ ቀርቷል በለዋል። 

ኮማንደሩ፤ በሕግ በማስከበር ሂደቱ የተፈጠረው ድንገተኛ የተኩስ ድምጽ ነዋሪዎችን በማደናገጡ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተቋርጦ ነበር፤ የንግድ ቤቶችም ተዘግተው ነበር ብለዋል። ትላንት የካቲት 24/2016 ዓ.ም ጀምሮ ግን የትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ ጀምሯል ነው ያሉት።  የንግድ ቤቶችም እሁድ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ከተዘጉት በስተቀር ክፍት ኾነው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል። 

“በባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር አሁን ላይ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሷል” ነው ያሉት ኮማንደር ዋለልኝ “ሕዝቡ ሰላሙ እንዲከበርለት አጥብቆ ይሻል” ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button