ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከወራት መዘግየት በኋላ የወሎ እና ደባርቅ ዩኒቨርስቲዎች መደበኛ ተማሪዎቻቸውን መቀበል ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ከወራት መዘግየት በኋላ የወሎ እና ደባርቅ ዩኒቨርስቲዎች መደበኛ ተማሪዎቻቸውን መቀበል መጀመራቸውን አስታወቁ። ወሎ ዩኒቨርስቲ ከአራት ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን መቀበሉን የአሚኮ ዘገባ ያሳያል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ.ም ለተቀበላቸው ከአራት ሺ በላይ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው ሊከተሏቸው የሚገቡ ሕግ እና ደንቦች ላይ ያተኮረ ገለጻ መሰጠቱን የጠቆመው ዘገባው ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው የዩኒቨርሲቲውን ሕግ እና ደንብ በተገቢው መንገድ ተረድተው በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አወል ሰይድ ለተማሪዎቹ በተደረገው አቀባበል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ማሳሰባቸውን አመላክቷል።

በተመሳሳይ ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎችን መቀበል መጀመሩን አሚኮ በዘገባው አስታውቋል። ዩኒቨርስቲው 1 ሺህ 500 ነባር ተማሪዎችን መቀበል ጀምሯል ሲሉ የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አስማማው ዘገየ (ዶ/ር) መግለጻውን አስታውቋል።

የክልሉ የሰላም ሁኔታ የተረጋጋ መኾኑን ተከትሎ ለተማሪዎች ጥሪ ማድረጋቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር አስማማው ገልጸዋል ያለው ዘገባው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ ችግር እንዳያጋጥም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ለቅድመ ጥንቃቄ በየመንገዱ የጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እያደረጉ መኾኑን አስረድተዋል ብሏል፡፡

በግቢው ውስጥ ተማሪዎች የሚገለገሉባቸው ቁሶች ዝግጁ መኾናቸውን እና ከኢንተርኔት አገልግሎት ጋር ተያይዞም በገመድ አማካኝነት የሚሠራ ኢንተርኔት ክፍት መደረጉን ገልጸዋል ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button