ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊላድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ወደ ተግባር ለመቀየር እንዳትሞክር ሲሉ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አስጠነቀቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14/2016 ዓ.ም፡- የሶማሊው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ማህሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሊላድ ጋር የደረሰችውን የባህር ዳርቻ ባለቤትነት ስምምነት ወደ ተግባር ለመቀየር ምንም አይነት እንቅስቃሴ ለማድረገ እንዳትሞክር ሲሉ አስጠነቀቁ።

ፕሬዝዳንቱ ከአልጀዚራ ጋር ባካሄዱት ቃለምልልስ  ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ደረስኩ ባለችው ስምምነት መሰረት የምታገኘውን የባህር ላይ ዳርቻ መሬት ለመጠቀም እና ማንኛውንም ንብረቷን ልታንቀሳቅስ የምትችለው የሶማሊያ ግዛትን አቋርጣ በማለፍ ብቻ ነው ሲሉ ገልጸው ይህንንም እንድታደርግ አንፈቅድም ብለዋል።

እስካሁን ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ግዛት ምንም አይነት እንቅስቃሴ አላደረገችም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ካደረጉ ግን ያኔ የተለየ መልክ ያለው ችግር ይፈጠራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የግብጽ ሚሊተሪ ወደ ሶማሊያ እንዲገባ በሚያቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ከግብጽ መንግስት ጋር አልተወያየንም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ነግር ግን በአሁኑ ሰአት በእኛ እምነት የተፈጠረው ችግር በዚያ ደረጃ ላይ አይደለም፣ ነገር ግን ወደ ለየለት ሁኔታ እንዳይገባ ነው ኢትዮጵያን እያስጠነቀቅን ያለነው፣ አትሞክሩት እባካችሁ ያልነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ከመፈራረማቸው ቀናት በፊት በጂቡቲ አግኝቻቸው ስለሶማሊያ አንድነት ብቻ ነበር ያወሩኝ፣ ደብቀውኛል እንጂ ፍንጭ አልሰጡኝም ሲሉ በመግለጽ ፕሬዝዳንቱ ጠ/ሚኒስትር አብይን ተችተዋል።

ሁሉንም አሸናፊ ሊያደርግ የሚችል መፍትሔ ይኖር ይሆን ተብለው የተጠየቁት ፕሬዝደንት ሀሰን ኳሷ በኢትዮጵያ እጅ ናት የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ መሃሙድ ጥያቄው ኢትዮጵያ የወደብ አቅርቦት ማግኘት አለባት ወይስ የለባትም የሚለው አይደለም፤ ኢትዮጵያ የወደበ አቅርቦት እንድታገኝ እንፈልጋለን፣ ይህ የሚያጠያየቅ አይደለም ሲሉ ገልጸው ከኢትዮጵያ ጋር የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ለመደራደር ዝግጁ ነው ብለዋል፤ ነገር ግን ቁራሽ መሬት በመውሰድ የሚሞከር ከሆነ ምንም አይነት ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ አይደለንም ሲሉም አብራርተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢትዮጵያ ለውይይት፣ ለድርድር እንዲሁም ለመነጋገር የሚገፋፋ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይጠበቅባታል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ መሃሙድ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በካይሮ ጉብኝት ማካሄዳቸው እና ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር መምከራቸውን መዘገባችን ይታወሳል። የሶማሊያውን ፕሬዝዳንትን ሀሰን ሸክ መሀሙድን በቤተመንግስታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በኢትዮጵያ ላይ የቀጥታ ዛቻ መሰንዘራቸውም በዘገባችነ ተካቷል። አልሲሲ ከሰነዘሩት ዛቻ መካከል “ለኢትዮጵያ ያለኝ መልዕክት የሶማሊያን ቅንጣት መሬት ለመቆጣጠር መሞከር ማንም የሚቀበለው አለመሆኑን ነው” የሚለው ይገኝበታል።

ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ መሃሙድ ከካይሮው ጉብኝታቸው በኋላ ወደ ኳታር ማቅናታቸውም ተዘግቧል። በኳታር ይፋዊ ጉብኝት ያካሄዱት ፕሬዝዳንቱ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስለጣናት ጋር በሀገራቱ ግንኙነት ዙሪያ መወያየታቸው እና በተለይም በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል ስለተደረሰው ስምምነት መምከራቸው ተጠቁሟል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button