ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ከእንግዲህ በኋላ ከፌደራል መንግስት ጋር በፕሪቶርያው ስምምነት ዙሪያ የማደርገው ውይይት በአፍሪካ ህብረት በኩል ነው – የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21/2016 ዓ.ም፡- የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር በፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ከፌደራል መንግስቱ ጋር የሚያደርገው ውይይት በአፍሪካ ህብረት በኩል ብቻ እንዲሆን መወሰኑን አስታወቀ።

ግዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ትላንት የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም አመሻሽ ላይ አካሄድኩት ባለው ስብሰባ በፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ዝርዝር ውይይት ማድረጉን ገልጿል።

የፕሪቶርያው ስምምነት በተሟላ መንገድ እንዲተገበር በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት የነበረው “የአፍሪካ ህብረት ፓናል” በአስቸኳይ ስራ እንዲጀምር ሲል ጠይቋል።

ከፌደራል መንግስት ጋር በመወያየት ችግሮችን ለማቃለል፣ መተማመን ለመፍጠር በተወሰነ ደረጃ እየሰራሁ መጥቻለሁ ያለው ግዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ የትግራይ ህዝብ ጥያቄዎች በተሟላ መንገድ ለመመለስ እንዲያስችል በሚል የውይይት አካሄዱ በሁሉቱ አካላት በፌደራል መንግስቱ እና በግዜያዊ አስተዳደሩ መሆኑ ቀርቶ ቀጣይ ውይይቶች በአፍሪካ ህብረት ፓኔል በኩል እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል።

ከግዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ከፕሪቶርያው ስምምነት ማግስት እስክ አሁን የታዩ ለውጦችን በመጠበቅ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በቆራጥነት መስራት ዋነኛ ምርጫው መሆኑን አመላክቷል፤ በቀጣይም ሰላማዊ የትግል ስልትን በአማራጭነት በመጠቀም በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራ ገልጿል።

የትግራይ ክልል ግዛታዊ ወሰን እንዲከበር በፕሪቶርያው ስምምነት እና በኢፌዲሪ ህገመንግስት መሰረት ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የጠቆመው ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስካሁን ከፌደራል መንግስት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ የተደረሰ ሁለትዮሽ የአተገባበር ስምምነት አለመኖሩን አስታውቋል።

በክልሉ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት የትግራይ ግዛታዊ አንድነት ሙሉ በሙሉ ሳይሸራረፍ ሲከበር፣ በትግራይ መሬት ላይ የሚገኙ የአማራ ታጣቂዎች እና የኤርትራ ሰራዊት ሙሉ በሙሉ ሲወጡ፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው የዕለት ተዕለት ስራቸውን ማከናወን ሲችሉ ነው ሲል ገልጾ በአጠቃላይ የፕሬቶርያው ስምምነት ሳይሸራረፍ ሲተገበር ብቻ ነው ብሏል። በመሆኑም የፌደራል መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ሲልም ጠይቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በቀጣይ አደራዳሪዎች በተገኙበት በሚካሄደው ስብሰባ የጋራ ስምምነት ላይ በመፈጸም የትግራይ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማስቻል በጽኑ እታገላለሁ ብሏል። በተናጠል ውሳኔ በትግራይ ህዝብ ላይ  አላስፈላጊ ተጽእኖ እና ጫና ለማሳደር የሚደረግ እንቅስቃሴ ትክክል ባለመሆኑ በፍጥነት እንዲታረም ሲል ጠይቋል፤ ጨናው ምን እንደሆነ ግን አላብራራም።

በፕሪቶርያው ስምምነት እንዲደረስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ኢጋድ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች ወዳጅ ሀገራት ሚናቸው ከፍተኛ ነበር ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ አሁንም ፓናሉ ስራውን በአስቸኳይ እንዲጀምር የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button