ዜናማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ከጋርዱላና ኧሌ ዞን ለህዳሴ ግድብ ዛፎች ምንጣሮ ወደ አማራ ክልል ያመሩ 285 የጉልበት ሰራተኞች ታጣቂ ቡድኖች መታገታቸው ተገለጸ 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28/ 2016 ዓ/ም፦ ከደቡብ አትዮጵያ ክልል ጋርዱላ እና ኧሌ ዞን ለህዳሴ ግድብ ዛፎች ምንጣሮ ወደ አማራ ክልል ያመሩ 285 የጉልበት ሰራተኞች “በታጠቁ የፅንፈኛ” ቡድኖች መንገድ ላይ መታገታቸውን የጋርዱላ ዞን አስተዳደር ምክር ቤት አስታወቀ። 

የጋርዱላ ዞን አስተዳደር ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ኩናሎ የኢትዮጵያ ኤሌክትርክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አካባቢ ለሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሐይቅ የሚፈጠርበት ቦታ ላይ ዛፎችን መቁረጥን ጨምሮ ጫካውን የመመንጠር ስራዎችን ለመከወን ጨረታ ማውጣቱን እና ኒኮትካ ኮንስትራክሽንና ትሬድንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የተባለ ድርጅት ጨረታውን ማሸነፍፉን ገልጸዋል።

ኒኮትካ ኮንስትራክሽንና ትሬድንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ከደራሼ ወረዳ የሠረተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ሰራተኞች ለመቅጥር ስምምነት በመፈፀም ጽ/ቤቱ የሰው ኃይሉን ከጋቶ፣ አቴያ፣ ግራሼ፣ ሽላሌ እና ከሆልቴ ቀበሌያት ላይ የስራ ማስታወቅያውን በማውጣት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ 246 ሰዎች ከቀበሌያቱ መመልመላቸውን የምክር ቤት ሰብሳቢ አስታውቀዋል።

በዚህም መሰረት ከደራሼ ወረዳ 246፣ ከኧሌ ዞን ደግሞ 39 የጉልበት ሰራተኞች በአንድ ላይ በ6 የድርጅቱ የህዝብ ማመላለሻ  አውቶብሶች ህጋዊ አካሄዶችን በመከተል ወደ አማራ ክልል ለስራ አሳፍሮ  ልኳል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጅ ሠራተኞቹ ተጉዘው አማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት ሲደርሱ በክልሉ ግዛት ውስጥ በማይታወቅ ሁኔታ “በታጠቁ የፅንፈኛ” ቡድኖች መንገድ ላይ ሊታገቱ ችለዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ምክር ቤትም በህዳሴው ግድብ  ልማት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እየሄዱ ባሉ ፊፁም ንፁሃን የሆኑ ዜጎች ላይ የተፈጠረው ክስተት አሳዛኝ እና አስነዋሪ መሆኑንና ተግባሩም ያልተገባ መሆኑን በጽኑ እንደሚያወግዘው አስታውቋል።

የዞኑ መንግስት፤ ሰራተኞቹ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት በወረዳው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ይፋ በተደረገው ማስታወቅያ መሠረት ተመልምለው በጊዜያዊ  የጉልበት ሠራተኛነት የውል ስምምነት ፈፅመው እየሄዱ ያሉ መሆናቸውን  የክልል መንግስታት ይወቁልኝ ብሏል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተለይም ሰራተኞቹ እንደዜጋ በየትኛውም የሀገርቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ በመስራት ሀብትን የማፍራት መብት ተጠቅመው በጉልበት ሠራተኛነት  የሚጓዙ መሆናቸው እና  ከጉልበት ሰራ ስምሪት ውጪ “የትኛውም ዓይነት የተለየ ተልዕኮ እንደሌላቸው” ብሎም ፊፁም ንፁሃን ዜጎች ሆነው ሳሌ በተሳሳቴ መንገድ እንደ አጥፍ ኃይል ተቆጥረው በምርኮኝነት ተይዘው ለአላስፈላጊ እንግልት መዳረጋቸው  አግባቢነት የለሌው ጉዳይ ነው ሲል ከሷል። 

የዞኑ አስተዳደር ምክር ቤት አክሎም ለሌላ ተልዕኮ እንደተላኩ አድርጎ በመውሰድ በምርኮኝነት በተለያዩ የፈስቡክ ገጾች እና በዩቱብ ላይ ጭምር በቪዲና በምስል የተራገበው መረጃ  ፊፁም ኃላፊትነት የጎደለውና ተገቢነት የለሌው ዕኩይ ተግባር መሆኑንም በአጽንኦት ገልጿል፡፡

በመጨረሻም የጋርዱላ ዞን አስተዳደር ምክር ቤት ዜጎቹ በሠላማዊ መንገድ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታችሁ አካላት ሁሉ ትኩረት ሰጥተው፤ ዜጎቹ በሠላማዊ ሁኔታ ወደ አካባቢያቸው እንድመለሱ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። አስ 

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button