ዜና

ዜና፡ የአውሮፓ ኅብረት የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ፕሮግራም የ16 ሚሊዮን ዩሮ ደጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/ 2016 ዓ/ም፦ የአውሮፓ ኅብረት በስምንት ክልሎች የሚገኙ 371 ሺህ 971 የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተን እና መልሶ ለማቋቋም (DDR) ፕሮግራም የሚውል የ16 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ። 

የአውሮፓ ኅብረት ለብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነርን ድጋፉን ያደረገው፤ በገንዘብ ሚኒስቴር በተከናወነው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ሲሆን የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋን ጨምሮ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር  ሮናልድ ኮቢ፣ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ራሚዝ አላብባራብ እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ሳሙኤል ዶ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት “በአገር አቀፍ ደረጃ በሚከወነው ትጥቅ ማስፈታት እና መበተን ፕሮግራም 15 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍን” የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ገልጸዋል።  ሚንስትሯ አክላም የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ፤ ለብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ያሉ ሌሎች አጋር አካላትን የሚጋብዝ መሆኑን መንግስት ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጻለች።

የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ከፊርማው ስነ ስርዓት በኋላ “የመጀመሪያውን መልሶ የሟቋቋም ስራ ለመጀመር ዝግጅታችንን እያጠናቀቅን በመሆኑ ሌሎች ወዳጆች እና አጋሮችም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ከአጠቃላይ 371 ሺህ 971 የቀድሞ ተዋጊዎች ውስጥ 75 በመቶ ወይም 274 ሺህ የሚሆኑት የሚገኙት በትግራይ ክልል ሲሆን፤ ቀሪዎቹ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ በቀድሞው ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎችም እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ማስታወቁ ይታወቃል።

አጠቃላይ የቀድሞ ታጣቂዎቹን መልሶ ለማቋቋም 850 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልገው የገለጸው ኮሚሽኑ ገንዘቡ ታጣቂዎቹን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ጀምሮ ከኅብረተሰቡ ጋር እስከመቀላቀል ድረስ ለሚሆነው ሥራ የሚውል መሆኑን አስታውቋል፡፡

በገንዘብ እጥረት ምክንያት በመጀመሪያው ዓመት 50ሺ ከትግራይ እንዲሁም 25 ሺህ ከሌሎች ክልሎች በአጠቃላይ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማደራጀት የተያዘው እቅድ ተግባራዊ ሳይሆን መቅረቱን ኮሚሽን የኮሙኒኬሽንና ዓለምአቀፍ ትብብር ዳይሬክተር አቶ ልዑልሰገድ በላይነህ ገልጸዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በቅርቡ ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚሰራውን ስራ ለመደገፍ ከአፍሪካ ህብረት ጋር የ1 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።

ለብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነርን ኮሚሽን የተቋቋመው በ2015 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሰረት ነው። አምባሳደር ተሾመ ከዚህ ቀደም ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደጉት ቃለ ምልልስ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የተፈረመው የጦርነት ማቆም ስምምነት ለኮሚሽኑ መቋቋም መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button