ዜናማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሰራተኞቹ በተሰጠው የምዘና ፈተና ከ15,151 ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብ ያሰመዘገቡት 6,517 ሰራተኞች ብቻ መሆናቸው ተገለጸ 

አዲስ አበባ ታህሳስ 30/ 2016 ዓ/ም፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሰራተኞች በተሰጠው የምዘና ፈተና ከ15,151 ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብ ያሰመዘገቡት 6,517 ሰራተኞች ብቻ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር)፣ በምዘና ፈተናው 4 ሺሕ 213 አመራሮች የተፈተኑ መሆኑንና ማለፊያ ውጤት ያመጡት 1 ሺህ 422 መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህም ከተፈተኑት አመራሮች ያለፉት 34 በመቶ የሚሆኑት መሆኑንም አንስተዋል። የተቀሩት አመራሮች ለማለፍ ማምጣት ከሚጠበቀባቸው ከ60 በመቶ በላይ ማምጣት አለመቻላቸው ተገልጿል። 

ፈተናውን የወሰዱ የሠራተኞች ቁጥር 10 ሺህ 257 ሲሆኑ ያለፉት 5 ሺህ 95 መሆናቸውን  አክለው ገልፀዋል። ይህም ሰራተኞች ለማለፍ ከሚጠበቀባቸው 50 በመቶ ውጤት ያማጡት ግማሽ የሚሆኑት መሆናቸው ተመላክቷል። 

ከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ መዋቅሮች ለሚሰሩ ሰራተኞቹ በሰጠው የምዘና ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡ ሰራተኞችና አመራሮች 15 ሺሕ 592 ለፈተናው የቀረቡት 15 ሺሕ 151 ሰራተኞች መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ገልጿል።

በሰራተኞቹ በኩል 681 የሚሆኑት በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች ምክንያት ፈተናውን ወስደው ያልታረመላቸው እንደሆኑም ተጠቅሷል። ፈተናውን እንዲወስዱ ከተጠበቁ ሰራተኞች መካከል 441 ሰራተኞች እንዳልተገኙም ተገልጿል።

ፈተናው ፍፁም ደህንነቱንና ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ መካሄዱንም ፈተናውን ያስተናገዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ገልፀዋል። 

አዲስ አበባ ከተማ አስተደደር የሰራተኞችን ብቃት እና ባህሪ ለመመዘን በሚል ለሰራተኞቹ ፈተናውን ቅዳሜ ታህሳስ 20 ቀን 2016 ዓ.ም መሰጠቱ ይታወሳል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button