ዜናማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በኢትዮጵያ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያሰፈልጋቸው ተገለጸ 

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 ዓ/ም፦  በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ ፣ደቡብ ፣ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደስፈልጋቸው  የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ በኢትዮጵያ አስታውቋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተመለከተ በጋራ በሰጡት መግለጫ ድርቁን ተከትሎ ካጋጠመው የምግብ እጥረት ባለፈ በነዚህ አካባቢዎች እንደ ወባ፣ ኩፍኝና ኮሌራ ያሉ በሽታዎች መከሰትን ጨምሮ በቀንድ ከብቶች ላይም ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ያለው ስር የሰደደ የሃብት ውስንነት እንዳለ ሆኖ ድጋፎቹን በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ለማዳረስ በአንዳንድ ኪስ አካባቢዎች የሚያጋጥመው የጸጥታ ችግር የሰብዓዊ እርዳታ የማከፋፈሉ ስራ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳረፉም መግለጫው አመላክቷል።

መንግስትና የረድኤት ድርጅቶች በአብዛኛው በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማዳረስ መቻላቸውም የተገለጸ ሲሆን በሦስት ዙር በተደረገ ድጋፍ በመንግስት ቢያንስ ለ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ መቻሉ ተመላክቷል።

በታህሳስ ወር አጋማሽ እንደገና በተጀመረው የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የሌሎች አጋር አካላት እገዛ በአማራ ፤በትግራይ፣ በሶማሌና በአፋር ክልሎች በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ወደ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል። የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የቅድሚያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በጥር ወርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

ለጋሽ አካላትም ይሄንኑ እንስቃሴ ለማገዝ ትኩረት እንዲሰጡ በመግለጫው ጥሪ  አቅርቧል። ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ በገንዘብ ድጋፍና በሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑም ተመላክቷል።

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግም የተቀናጀ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት አስፈላጊ መሆኑ በመግለጫው ጠቅሶ እንደ ወባ፣ ኩፍኝና ኮሌራ ያሉ በሽታዎች መከሰትን ጨምሮ በቀንድ ከብቶች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

መንግስትና የረድኤት ድርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታ በማድረስ በኩል ያላቸውን ልምድና የተጠናከረ የባለሙያ ስብስብ ለዚሁ ተግባር ለማዋል ዝግጁ መሆናቸውም መግለጫው አመልክቷል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button