ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ዩናይትድ ኪንግደም የኤርትራው አምባሳደር ከአገሯ ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

አዲስ አበባ፣ ጥር 10/2016 .ም፡ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በለንደን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት እስጢፋኖስ ሃብተማርያም ከአገሩ እንዲወጡ ማዘዙን ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ አስታወቀ።

የአምባሳደሩን መባረር በተመለከተ በይፋ የተሰጠ መግለጫ አለመኖሩን የጠቆመው ዘገባው የአምባሳደሩን ቦታ በመሸፈን በስራ ላይ የሚገኙት የኤምባሲው (ሚሲዮን) ከፍተኛ ተጠሪ በመሆን የሚሠሩት ሳሌህ አብዱላህ መሆናቸውን በለንደን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ድረ-ገጽን መረጃ ዋቢ በማድረግ አመላክቷል።

የዩኬ መንግሥት አምባሳደር እስጢፋኖስ ሃብተማርያም ላይ ከአገር እንዲወጡ የወሰደው እርምጃ፣ ኤርትራ ቀደም ብሎ ለወሰደችው ተመሳሳይ ውሳኔ ምላሽ መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮቹ እንደነገሩት ዘገባው አካቷል።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በኤርትራ የዩኬ አምባሳደር የሆነው የተሰየሙት ዲፕሎማት በኤርትራ መንግሥት አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ወደ አሥመራ መጓዝ ሳይችሉ መቅረታቸውን ያወሳው ዘገባው ይህንንም በተመለከተ የኤርትራ ባለሥልጣናት የዩኬ ተሿሚ አምባሳደር ወደ ምድብ ቦታቸው ገብተው ሥራቸውን እንደጂምሩ ለምን አስፈላጊውን ነገር እንዳላደረጉ የተሰጠ ምክንያት አለመኖሩን ጠቁሟል።

አሁን ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት የኤርትራው አምባሳደር እስጢፋኖስ ሃብተማርያም ላለፉት ስምንት ዓመታት አገራቸውን ወክለው ዩኬ ውስጥ ሲሠሩ መቆየታቸውንም አስታውሷል።

ምንም እንኳን የኤርትራው አምባደሳደር ከለንደን እንዲወጡ ቢታዘዙም ኤምባሲው መደበኛ ሥራውን እንደሚቀጥል የታወቀ ሲሆን፣ በአሥመራ የሚገኘው የዩኬ ኤምባሲም ለዜጎቹ የቆንስላ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ነገር ግን በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ የሁለቱም አገራት ጥምር ዜግነት ያላቸውን ሰዎችን ለመርዳት አዳጋች ሁኔታ እንዳለ ተነግሯል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button