ዜናፖለቲካ

ዜና: በትግራይ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከተፈጸመው ግፍ የተረፉ ዜጎች አሁንም ፍትህ አላገኙም - አምነስቲ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ በትግራይ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከተፈጸመው አስከፊ ወንጀሎች የተረፉ ዜጎች አሁንም ፍትህ አላገኙም ሲል አምነስቲ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የጦር ወንጀል፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ፈጽመዋል ሲል የአሜሪካን መንግስት ከአንድ አመት በፊት ውሳኔ ቢያሳልፍም አሁንም ምንም አይነት የፖሊሲ ለውጥ አላደረገም ሲል አምነስቲ በመግለጫው ተችቷል፤ ፍትህ እና ተጠያቂነት ለማስፈን የወሰዳቸው አንዳችም እርምጃ የለም ብሏል።

ትርጉም ባለው አዲስ ፖሊሲ ያልተደገፈ፣ ጭካኔ የተሞላበት ግፍ እና ወንጀል ተፈጽሟል ብሎ ውሳኔ ማሳለፍ ብቻውን ለወንጀሉ ተጠቂዎች እና ከግፉ ለተረፉ ዜጎች የሚፈይደው ትርጉም ያለም ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዩኤስኤ ዳይሬክተር ኬቲ ሂክሰን መግለጻቸውን አካቷል።

የአሜሪካ መንግስት ከወንጀሉ የተረፉ ተጠቂዎች ፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለሚያቀርቡት ጥያቄ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ማለታቸውንም አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱም ከአመት በፊት ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲከልስ የጠየቀው አምነስቲ በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ በማካተት ፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ብሏል።

ልክ የዛሬ አንድ አመት መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን የሀገራቸው መንግስት በትግራዩ ጦርነት የተሳተፉ ሀይሎች ሁሉም የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቀው እንደነበር አምነስቲ አስታውሷል። የኤርትራ ሰራዊት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል፣ የአማራ ታጣቂ ሀይሎች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ፈጽመው ተገኝተዋል ሲሉ መናገራቸውን አመላክቷል።

የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ወንጀል ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ እና ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አላደረገም ሲል ተችቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት የመካላከያ ሀይሉ እና የፋኖ ታጣቂዎች በመዋጋት ላይ መሆናቸውን የጠቀሰው አምነስቲ በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት የመከላከያ ሀይሉ የፈጸማቸው ወንጀሎች የጦር ወንጀል የመሆን እድል እንዳላቸው ያሰባሰብኩት መረጃ ያሳያል ብሏል።

በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት ሳቢያ ከባለፈው አመት ነሃሴ ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን የጠቀሰው አምነስቲ ነጻ ጋዜጠኞች ስለ ግጭቱ እንዳይዘግቡ ተከልክለዋል፣ ሙከራ ያደረጉም ለእስር ተዳርገዋል ሲል ገልጿል። የሀገሪቱ ባለስልጣናት በክልሉ የተላለፈውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ለማሰማት የሚደፍሩ ሰዎችን ለማፈን ተጠቅመውበታል ሲል ተችቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ በሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበራት ላይ ማስፈራራት እየፈጸመባቸው መሆኑን የተመለከቱ ሪፖርቶች እንደደረሱት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል በአማራ ክልል ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ ተግባር ከመፈጸም እንዲቀጠብ ለማድረገ የሚያስች አስቸኳይ ስራ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ዋና ጸሐፊ አንቶኒ ብሊንከን ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን እንዲሰሩ አሳስቧል።

አንቶኒ ብሊንከን መስሪያ ቤታቸው ከአመት በፊት ያሳለፈውን ውሳኔ በማስፋት በአሁኑ ወቅት ግጭት እየተካሄደባቸው ባሉት የኦሮምያ እና አማራ ክልሎችን ማካተት ይገባዋል ያለው ተቋሙ  ተጠያቂነት እና ፍትህ እንዲሰፍን በአፋጣኝ ሊሰራ ይገባዋል ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button