ጥልቅ ትንታኔፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ ህወሓት፤ መጻኢ እጣፈንታው ያልታወቀው ፓርቲ 

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12/2016 ዓ/ም፦ በ1966 ዓ.ም የካቲት ወር ነበር ንጉሳዊ ስርአቱ ተገርስሶ ወታደራዊ ደርግ ወደ ስልጣን የመጣው። ለንጉሱ ስርአት መውደቅ ዋነኛ ምክንያት የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነው፤ ከሌሎቹ አመጾች እና ምክንያቶች መካከል ጎልቶ የሚወጣም ነው። አብዮቱ በፈነዳ በአመቱ የትግራይ ወጣቶች በደደቢት፤ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መስርተው አሁን ላይ ፓርቲው 50 አመት ሊሞላው አንድ አመት ብቻ ቀርቶታል። 

የፈነዳው አብዮት 17 አመታትን ደርግ ሀገሪቱን እንዲገዛ አመቻችቷል። በአብዮቱ በፈነዳ ማግስት የተቋቋመው ህወሓት ደግሞ ከ17 አመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ደርግን በመጣል የሀገሪቱን ስልጣን ከተቆጣጠሩ ሀይሎች ዋነኛው ለመሆን በቅቷል። ስልጣን ይዞም ለ27 አመታት ኢትዮጵያን የመራው ፓርቲው፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ለሁለት አመታት ከተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ጋር ተያይዞ በፈተና እየተናጠ ይገኛል።

ጦርነቱን ተከትሎ ዕውቅናው ተሰርዞ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት፤ በትግራይ እና በአጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተውን ጦርነት ለመቋጨት በደቡብ አፍሪካ በተደረገው በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት፤ የሽብርተኘነት ፍረጃው የተነሳለት ቢሆንም ዕውቅናው ግን ገና አልተመለሰለትም። 

በፕሪቶርያ የተፈረመውን ስምምነት ከትግራይ በኩል የፈረመው ህወሓት መሆኑን ተከትሎ ለስምምነቱ ስኬት ሲባል ዕውቅናው ይመለስለታል የሚለው ሀሳብ ሚዛን እየደፋ የመጣ ይመስላል። የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባሉ እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ለክልሉ ጋዜጠኞች በሰጡት ቃለምልልስ ይህንኑ አረጋግጠዋል። ለዚህም በሚመስል መልኩ በዚህ ሳምንት ጉባዔ እያካሄደ ይገኛል።

የአድሜ ጠገቡን ህወሓት በ49 ዓመታት ጉዞው ያሳካቸውን ነገሮችን በተመለከተ የጠይቅናቸው የፖለቲካ ምሁራን በመጀመሪያው ምዕራፍ ከምስረታው እስከ ደርግን መገርሰስ ስኬታማ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።  

ህወሓት በጉዞው ምን አሳካ? ስንል የጠየቅናቸው፤ የህወሓት የፕሮፓጋንዳ ክፍል ኃላፊው እያሱ ተስፋይ፤ ድርጅቱ፤ በተደራጀ አመራር እጦት ለበርካታ ዘመናት ሲሰቃይ የነበረውን የትግራይ ህዝብ በተደራጀ መንገድ እንዲታገል ማስቻሉ አንዱ እና ስኬቱ ተደርጎ ሊወሰድለት የሚገባው ነው ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም የትግራይን ህዝብ ጥያቄዎች መልክ አስይዞ አደራጅቶ በማቅረብ እና በማታገል ምላሽ እንዲያገኙ ጥሯል ሲሉ ገልጸው ይህም ስኬቱ ነው ብለዋል።

ፓርቲውን ከልጅነታቸው እስከ ጡሮታ ዘመናቸው ያገለገሉት፣ በተለያዩ የፌደራል ተቋማትም በአመራርነት የሰሩ እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ሁነው በማገልገል ያሉት አቶ ሀዱሽ ካህሱ፤ በበኩላቸው ፓርቲው፤ ይዞት ከተነሳው አላማ፣ ግብ፣ ከተከተለው እስትራቴጂ እና ታክቲክ በምዕራፍ ከፋፍለህ ካየኸው በሁሉም ምዕራፎች ስኬቶች አስመዝግቧል ሲሉ ገለጸዋል። “ዋነኛው ስኬቱ ግን የትግራይን እና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል መቀየር ነበር፤ በአመዛኙም አሳክቶ ነበር ሲሉ” ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የትግራይ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪው ዶ/ር ሙዑዝ ግደይ፤ የትግራይ ህዝብ ህዝባዊ እንቢታ መገለጫ የሆነ አንድ ህዝባዊ አብዮት ማቀጣጠል ችሏል ብለዋል። 

“መልክ ያለው ፍልስፍና ያለው ወታደራዊ ቁመና ያለው የፖለቲካ ፕሮግራም ያለው ሁኖ እንዲወጣ ከማድረግ አንጻር እንዲሁም ጠንካራ መሪ እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር የመጀመሪያው ምዕራፍ ከብረት ትግሉ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ ያለውን ያየን እንደሆነ በሚገርም ሁኔታ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ጭምር የህዝባዊ እምቢታ፣ ፍትሃዊ ትግል ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነበር” ብለዋል። ህወኃት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ዘመናዊነትን ማስተዋወቅ ዋነኛ አላማው እንደነበር ገልጸው፤ የስርዓቱ ውድቀት ከሌሎች ብሔር ብሔሮች ጋር ሁኖም ቢሆን የአንበሳውን ደርሻ የትግራይ ህዝብ ይይዛል ሲሉ ጠቁመዋል። 

ከ1983 በፊት የነበረው ህወሓት የህዝብ ድርጅት ነበር ብሎ መናገር ይቻላል ያሉን የውድብ ናጽነት ትግራይ (ውናት) ፓርቲ ሊቀመንበሩ ዶ/ር ደጀን “የደርግን ስርአት ከህዝቡ ጋር በመሆን ከገረሰሱ በኋላ ግን ትግሉን ጠልፈዋል” ሲሉ ኮንነዋል። የትግራይ ህዝብ የታገለው መብቱን ለማስከበር እና ትግራይን ነጻ ማውጣት ነበር ሲሉ የገለጹልን ዶ/ር ደጀን “ሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ከፈለጉ ራሳቸውን ነጻ ያውጡ ብሎ ነበር” ሲሉ አውስተዋል። በ17 አመቱ ትግል ታላላቅ ውጤቶች መጥተዋል ብለዋል።

ለአዲስ ስታንዳርድ አስተያየታቸውን የሰጡ የክልሉ ልሂቃን የወታደራውው ስርአት የደርግን ውድቀት፣ ህገመንግስት መጽደቁ፣ ሁሉም ብሔሮች እውቅና መሰጣጣታቸው እና በጤና በትምህርት እንዲጉም በኢኮኖሚ እድገት ዙሪያ ያመጣውን ለውጥ በአመዛኙ እንዲሁም “ከነእንከኖቹም ቢሆን በስኬትነት ሊታይለት እንደሚችል” ጠቁመዋል።

“የትግራይን ህዝብ ታግየ አታግየ አንድ ምዕራፍ አሻግሪያለሁ” ሲል የሚገልጸው ህወሓት፤ እንደ ፓርቲ ህልውናው አደጋ ላይ የወደቀው እና የትግራይን ህዝብ በጦርነት ለእልቂት የዳረገው ምን ባያሳካ ነው? ስንል የጠየቅናቸው ልሂቃኑ የያራሳቸውን ምልከታ አጋርተውናል።

“ህወሓት ከዚህ በኋላ አይድንም የሚድንበት እድልም የለውም፤ የፓርቲው አሁናዊ ሁኔታ በሞት እና በህይወት ለመኖር የሚደረግ ትግል ነው”_ የውድብ ናጽነት ትግራይ (ውናት) ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ደጀን

የድርጅቱ የፕሮፓጋንዳ ክፍል ሃላፊ እያሱ ተስፋይ ደግሞ፤ “ህወሓት የትግራይ ህዝብ የሚፈልገውን ልማት ማረጋገጥ አልመቻሉ፣ መልካም አስተዳደር ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንዲተገበር አለማድረጉ፣ የተጀመረ እንቅስቃሴ አድርጓል እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አለመምጣቱ ያላሳካቸው ጉዳዮች መሆኑን እንደፓርቲ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል።  በልማቱ የተሻለ ቢሆን እንኳ በመልካም አስተዳደር ግን ወደ ኋላ የቀረ ነበር ያሉት ሃላፊው፤ በዴሞክራሲ አኳያ በተለይም በተቋማት እና ህዝብን በማሳተፍ ረገድ  ያላሳካቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዶ/ር ሙዑዝ ጊደይ በበኩላቸው፤ “ድርጅቱ፤ ከ1993 ዓ.ም በኋላ ወደ ፖለቲካዊ አምባገነንነት ያደላ ስርዓት ገንብቷል ይህ ደግሞ የትግራይን ህዝብ እንዲጠቃ በማድረጉ ረገድ ሚና ነበረው” ሲሉ አብራርተዋል።

“የትግራይ ህዝብ የሚመኛትን ኢትዮጵያ መፍጠር፣ ከሌሎች ህዝቦች ጋር የሚገባውን ጥቅም እና መብት ተከብሮለት ማየት የሚሉ ግቦችን አላሳካም ማለት ይቻላል” ብለዋል።

የውድብ ናጽነት ትግራይ (ውናት) ፓርቲ ሊቀመንበሩ ዶ/ር ደጀን፤  “ህወሓት በ1983 ዓ.ም የትግራይ ህዝብ ያገኘውን ድል በመጥለፍ ህገመንግስት አጸደኩ ብሎ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ቀበራት” ሲሉ ተችተዋል። 

“ከ1983 በኋላ ህወሓት ትግራይ ትቶ ሁሉም ነገሩ ኢትዮጵያ ሆነ፣ የትግራይ የሆኑትን በሙሉ ደመሰሳቸው ወደ ኢትዮጵያ አዞራቸው” የሚሉት  ሊቀመንበሩ፤ “ትግራይ የሚያልፍላት ኢትዮጵያ ሲያልፍላት ነው በሚል ጎትተው እዚህ አደረሱት ህዝቧንም ባለሀብቷንም ለስደት የዳረገ ስርአት ነበር የገነባው” ብለዋል።

ህወሓት አሁን በምን ቁመና ላይ ይገኛል?

የህልውና አደጋ ተየጋረጠበት ህወሓት በምን ቁመና ላይ ይገኛል ስንል የጠየቅናቸው ልሂቃኑ በሰጡን ምላሽ “በከፍተኛ አደጋ” ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የትግራይ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪው ዶ/ር ሙዑዝ ግደይ፤ ህዝባዊነት ቁርጠኝነት ቅንነት እና አቅምን መሰረት አድርገን የህወሓትን አሁናዊ ቁመና ካየነው “ሞቷል” ሲሉ ተናግረዋል። “በአቅም አንጻር ካየን ህወሓት አቅሙ ሞቷል፣ ከቀድሞ መሪው አቶ መለስ ዘናዊ በኋላ የአመራርነት ክፍተት መፈጠሩን አራሳቸው የፓርቲው አመራሮች በተደጋጋሚ አምነዋል፤ ከቅንነት አንጻርም ካየኸው ቅንነታቸውን አጥተዋል፤ ህዝባዊነትን ካየህ እንጥፍጣፊ ላይ የሚገኝ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

አክለውም “ጠንካራ የህዝብ ድጋፍ ስላለው እና ጠንካራ እያለ የሰራቸው ስራዎች ድጋፍ ሆነውት ነው አሁን ያለ የሚመስለው። የመቃናት እና የመዳን እድል አለው ብየ አላስብም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

“በፓርቲው ውስጥ በአሁኑ ወቅት የመስመር ችግር አላጋጠመንም፤ የተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ ብንለው ይሻላል” _ የህወሓት የፕሮፓጋንዳ ክፍል ኃላፊ እያሱ ተስፋይ

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ሀዱሽ ካህሱ ግን በዚህ አይስማሙም። “በህዝባዊነቱ እና በህዝባዊ አላማው ጸንቶ ይገኛል ሲሉ” ገልጸዋል። 

“ህወኃት በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ ነው የመጣው፣ በተመሰረተ በስድስተኛ ወሩ ነበር ፈተና የገጠመው፤ ብዙ ፈተናዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተሻግሮ ነው የመጣው” ሲሉ በመግለጽ፤ የአሁኑንም ፈተና ይሻገረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል።

የተዋቃሚው የውድብ ናጽነት ትግራይ (ውናት) ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ደጀን ግን “ህወሓት ከዚህ በኋላ አይድንም የሚድንበት እድልም የለውም” ሲሉ ገልጸው የህወሓት አሁናዊ ሁኔታ “በሞት እና በህይወት ለመኖር” የሚደረግ ትግል ላይ ነው ሱሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ምልከታቸውን አጋርተዋል። በአሁኑ ወቅት ህወሓት “መሰረቱን ያጣ እና የተንሳፈፈ” ድርጅት ነው ብለዋል።

የህወሓት የፕሮፓጋንዳ ክፍል ሃላፊው እያሱ ተስፋይ በበኩላቸው ፓርቲው ውስጣዊ ችግር ያለበት ቢሆንም ችግሮቹን ለመፍታት እየተጣጣረ ነው ብለዋል።  “ህዝቡ ፓርቲው በሚፈልገው መንገድ እየሄደ እንዳልሆነ ያውቃል፣ ተቋማዊ ሁኔታውን ለማስተካከል እየጣረ ያለ ፓርቲ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

የህወሓት አሁናዊ ሽኩቻ የመስመር ወይንስ የስልጣን?

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች የህወሓት አመራሮች በሽኩቻ ተጠምደዋል ሲሉ ይደመጣሉ። ከሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ጀምሮ እስከ ስራ አስፈጻሚ አባሉ እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በተለያየ መንገድም ቢሆን ሽኩቻ መኖሩን ገልጸዋል። 

በቅርቡ የቀድሞ የፓርቲ አመራሮች እና በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከፓርቲው ጋር እድሚያቸውን ያሳለፉ እንዲሁም በትግራይ በተካሄደው ጦርነት የተሳተፉ በወታደራዊ አመራሮች የተካፈሉበት ግምገማ ሁሉ አካሂዷል። በዚህ ሳምንትም ፓርቲው ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል። 

የውስጥ ሽኩቻው የስልጣን ወይንስ የመስመር (የአይዲዮሎጂ) ስንል የጠየቅናቸው ዶ/ር ሙዑዝ “ሁለቱም አይደለም” ሲሉ በመግለጽ “የፖለቲካዊ መበስበስ ማሳያ ነው፤ የግለሰቦች እና የቡድን ፍላጎት ለማስከበር የሚደረግ ሽኩቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። የመስመር ነው የስልጣን ነው ሊባል የሚበቃ አይደለም ያሉን ሙዑዝ ጊዴይ ሙሉ በሙሉ “የፖለቲካ መበስበስ ማሳያ ነው” ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተውናል።

የህወሓቱ እያሱ ተስፋይ በበኩላቸው፤ “በፓርቲው ውስጥ በአሁኑ ወቅት የመስመር ችግር አላጋጠመንም” ሲሉ ገልጸው፤ የተፈጠረው “የስልጣን ሽኩቻ ብንለው ይሻላል፣ ለህዝብ የመወገን እና ያለመወገን ጉዳይ ነው” ብለዋል።

“መፈክራችን፤ መስመር ነው ሀይላችን፣ ህዝብ ነው ሃይላችን ነው የሚለው፣ ይህም ማለት መስመሩ ህዝብ  መሆኑን ለማመላከት እና ህዝባዊነቱን ለማሳየት ነው። መስመር የሚባል ከህዝብ የተለየ ግኡዝ ነገር የለንም፣ ህዝባችንን ይዘን የማንፈታው ችግር የለም” ሲሉ ለፓርቲያቸው ያላቸውን እምነት አስታውቀዋል።

እንደ ሀዱሽ ካህሱ ምልከታ፤ ችግሩ የሚታየው በማዕከላዊ ኮሚቴው ላይ እንጂ ካድሬው ላይ አይደለም። “የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እና ስለጣኑን እንደ መተዳደሪያው እና መኖሪያው አድርጎ የተቀመጠ ሀይል አለ፤ ይህም ማለት ሽኩቻው የስልጣን እንጂ የመስመር አለመሆኑን ነው የሚያመላክተው፣ የመስመር ችግር አለ የሚል አስተያየት እስካሁን አልተሰማም” ብለዋል።

“የስትራቴጂካዊ አመራር እጦት ችግር ነው” ያሉን ሀዱሽ ካህሱ፤ “ሌላኛው ችግር ፓርቲው ጉባኤ ካካሄደ ቆይቷል፣ ማድረግ የነበረበት ግዜ አልፏል፣ መታገልም አቁሞ ነበር ማለት ይቻላል። በህዝቡ ላይ በታወጀው የዘር ማጥፋት ጉዳይ ተጠምዶ ስለነበር ውስጡን አላየም፤ ችግሮቹ በነዚህ ምክንያት እየገኑን የመጡት” ብለውናል።

ህወሓት ከክልሉ አልፎ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ሚና የመጫወት ቁመና ይኖረዋል?

ህወሓት የሽብርተኝነት ፍረጃው ቢነሳለትም በምርጫ ቦርድ የተነፈገው ህጋዊ እውቅናው አልተሰጠውም። በቅርቡ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ለክልሉ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ህጋዊ ህልውናው በቅርቡ እንዲመለስ ጠ/ሚኒስትሩ አዘዋል፣ ይህንንም እንዲያስፈጽሙ ለፍትህ ሚኒስትሩ ኃላፊነት ተሰጥቷል ሲሉ ተደምጠዋል። 

ይህ ከሆነ ህወሓት በክልሉ ፖለቲካ፣ ከዚያም አልፎ እንደ ሀገር አዲስ ሚና የመጫወት እድሉን ያገኛል ማለት ነው? አቅምስ አለው? ስንል የጠየቅናቸው ዶ/ር ሙዑዝ፤ ፓርቲው “አቅሙን አሟጦ ጨርሷል ማለት እንችላለን” ሲሉ ገልጸው፤ “አሁን ብልጭ ብልጭ እያለች የምትታየውም ከራሱ የመጣ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም በህዝቡ ላይ የፈጠረው እምነት በታሪክ ያለው የጎላ ቦታ የትግራይ ህዝብ ለፖለቲካ አንድነት ካለው ቅንነት የተነሳ እንጂ በራሱ አይደለም” ብለዋል።  “ተመልሶ የመምጣት እድሉ እጅግ የመነመነ ነው” ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተውናል። 

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ እና የፕሮፓጋንዳ ክፍል ሀላፊው እያሱ ተስፋይ ግን በዚህ አይስማሙም። ህወሓት ህዝባዊ ፓርቲ ነው ሲሉ ገልጸው፤ “ህዝቡ የት ሂዶ ነው አቅሙን የሚጨርሰው፣ ግለሰብ አቅሙን ሊጨርስ ይችላል፤ ህዝብ ግን አይመስለኝም” ብለዋል። ከድያስፖራው እስከ አርሶ አደሩ ድረስ የሚያሳትፍ መሆኑን መረሳት የለበትም ሲሉም አክለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button