ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” - የአማራ ክልል መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9/2016 ዓ.ም፡- የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ “ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሓት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” ሲል ኮንኗል።

የክልሉ መንግስት በመግለጫው “ህወሓት የመላ ኢትዮጵያ ጠላትና የደኅንነት ስጋት ነው” ሲል በመፈረጅ “ከዉጭ እና ከዉስጥ ጠላቶቻችን ጋር ተናብቦና ተቀናጅቶ በርካሽ ፖለቲካዊ ብያኔና ፍረጃ በጊዜያዊ አሥተዳደሩ ካቢኔ አማካኝነት መጋቢት 16/2016 ዓ.ም የአማራ ክልል ተማሪዎችን መማሪያ መጽሐፍ እንደ ሰበብ ተጠቅሞ በይፋ ጦርነት ማወጁና መቀስቀሱ ይታወቃል” ሲል አስታውሷል።

“ህወሓት ከጦርነት ውጭ ማሰብ የማይች ነው“ ሲል የገለጸው የክልሉ መንግስት መግለጫ “የአማራ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ ከትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር ጋር በፌዴራል መንግሥት አማካኝነት ውይይት” ሲያደርግ እንደነበር ጠቁሟል።

“ህወሓት ይህን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ አካባቢዎች ላይ ወረራ ፈፅሟል” ሲል አስታውቋል።

ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በማክበር በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን ከመወጣት ይልቅ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ በመጣስ የተለያዩ ጥፋቶችን ሲፈጽም ቆይቷል፤ አሁንም እየፈጸመ ይገኛል ሲል ተችቷል።

ስለሆነም የአማራ ክልል መንግሥት ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በማክበር በአጭር ጊዜ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ ጠይቋል።

ይህ የማይኾን ከኾነ የአማራ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድምና እህት ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ በመኾን ሀገርን ከማፍረስ መታደግና ሕዝባችንንም ከጥቃት ለመከላከል የምንገደድ ይሆናል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የክልሉ መንግስት “በየደረጃው ያላችሁ የፖለቲካና የጸጥታ መዋቅር አባላት” በሚል ባስተላለፈው መልዕክት “ዛሬም እንደ ትናንቱ በፅናትና በቁርጠኝነት ሕዝቡን በማደራጀት አካባቢያችሁን በመጠበቅ ታሪካዊ ኀላፊነታችሁን እንድትወጡ” ብሏል።

ለክልሉ ሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክት “ ከሐሰት ፕሮፓጋንዳ እና ሠርጎ ገቦች ራስህን በመጠበቅ ከክልል መንግሥትና በየአካባቢው ከሚገኙ አሥተዳደሮች ጋር የጠበቀ ቁርኝት በመፍጠር ጠላቶቻችን የከፈቱብንን ጥቃት ለመመከት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የድርሻህን እንድትወጣ” ሲል ጠይቋል።

“የፌደራል መንግሥት ህወሓት ከወረራቸው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ለቆ እንዲወጣ በማድረግ ሕዝባችንን ከጥፋት መታደግና የሀገራችንን ሉዓላዊነት ማስከበር ይገባል” ሲል አሳስቧል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button