ዜና

ዜና፡ በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል 500 ሚሊዮን ብር ያሳጡ 30 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25/ 2016 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ፣ ሸገር ከተማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ ሐዋሳ እና ጂማ ከተሞች  በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ላይ የተሰማሩ 30 ተጠርጣሪች ከ73 በላይ ማጭበርበሪያ መሳሪያ ጋር እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የፌደራል ፖሊስ አስታወቁ፡፡

ተቋማቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ በሀገር ደኅንነት ላይ ሥጋት በሚፈጥረው በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን ሲሰሩ የቆዩት የተለያዩ የግለሠብ ቤቶችንና ግቢዎችን በመከራየት መሆኑን ገልፀው ለዚሁ ሕገ ወጥ ተግባር ሲውሉ የነበሩ ከ200 ሺ በላይ የሳፋሪኮም እና ኢትዮቴሌኮም ሲም ካርዶች ተይዘዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በቁጥጥር ስር ከዋሉ የማጭበርበሪያ ጌትዌይ መካከልም በአንድ ጊዜ 127 የኢትዮቴሌኮም ወይም ሳፋሪኮም ሲም ካርድ መያዝ የሚችል መሣሪያ መገኘቱንም ጠቁሟል፡፡

በእነዚህ መሣሪያዎች የሚፈጸሙት የማጭበርበር ድርጊቶች ኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ማጣታቸውን አስታውቀዋል። በማጭበርበሪያ መሣሪያዎች የተነሳ በቴሌኮም አገልግሎት አሰጣጥ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡

የተቋማቱ የጋራ መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት መሣሪያዎቹን በመጠቀም ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ኢትዮ ቴሌኮም ወይም ሳፋሪኮም በዘረጋው ኔትወርክ ሳይሆን ራሳቸው በዘረጉት የማጭበርበሪያ ጌትዌይ ለደንበኞች የሚያቀርቡ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

በማጭበርበር ወንጀሉ ላይ የሚሳተፉ ግለሠቦች ከአለም ዓቀፍ ተዋንያን እስከ ሀገር ውስጥ ቤት አከራይ ድረስ ትስስር መፍጠራቸውን የተቋማቱ የጋራ መግለጫ አስታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎች መቀመጫቸውን ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎች ሀገራት ካደረጉ ዜጎች ጋር በመመሳጠር እና ተቀጥረው በመሥራት ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደተደረሰባቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጋራ መግለጫ ጠቁሟል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button