ዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በሶማሊያ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰባት ኢትዮጵያውያን ሰደተኞች ተገደሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28/ 2016 ዓ/ም፡_ በደቡብ ሶማሊያ ጌዶ ክልል በለድ ሃዎ ከተማ ባሳለፍነው እሁድ ጥር 26፣ 2016 ዓ/ም “የሀገሪቱን የጸጥታ ደምብ ልብስ የለበሱ” ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰባት ኢትዮጵያውን መገደላቸውን እና ሌሎች ስድት ሰዎች መቁሰላቸውን የስፍራው ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ። 

በታጣቂዎቹ የተገደሉት እና ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን “የኦሮሞ ተወላጆች” መሆናቸውንና በለድ ሃዎ ከተማ በጸጉር ቤት (የውበት ሳሎን) እና በተለያዩ የስራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ዜጎች መሆናቸውን አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረው ምንጭ ገልጿል። 

ነዋሪነቱን በሶማሊያ ያደረገ ስሙ እንዲገለጽ ያለፈለግ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ፤ ጥቃቱ ለኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው በለድ ሃዎ ከተማ ጥር 26 ከለሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ መፈጸሙን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።

“የሶማሊያ የጸጥታ ደምብ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ከለሊቱ 8፡00 ሲሆን የኦሮሞ ተወላጅ ቤቶች በመግባት በመሳሪያ ጥቃት መፈጸም ጀመሩ። በፈጸሙት ጥቃትም ሰባት ኦሮሞዎችን በጥይት ገድለዋል። ሌሎች ስድስት ሰዎችን ደግሞ አቁስለው ሄደዋል። ከቆሰሉት ውስጥ ሁለቱ በህይወት እና በሞት መካከል ይገኛሉ” ሲል ነዋሪው የተፈጠረውን ክስተት አስረድቷል።

በሶማሊያ ታጣቂዎች ከተገደሉት መካከል አራቱ ሴቶች፣ ሶስቱ ወንዶች መሆናቸውን የጠቀሰው ነዋሪው፤ ጥቃቱን ለማስቆም የሞከረች አንድ የሶማሊያ ሴትም መገደሏን ገልጿል።  አክሎም “በተፈጸመው ጥቃት እናት እና አባቱ የተገደሉበት ህጻን ይገኛል። ጋብቻ ከፈጸሙ አንድ ሳምንት የሆናቸው ባል እና ሚስትም በእለቱ ከተገደሉት መካከል ናቸው” ብሏል። 

ሌላኛው አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረው በሶማሊያ የሚኖር የኦሮሞ ተወላጅ፤ ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ በተፈጸመው ጥቃት 22 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ተናግሯል። 

ስደተኞቹ ጥቃት አድራሾቹ “የሶማሊያ ጦር የደምብ ልብስ የለበሱ” መሆናቸው ቢገልጹም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የበለድ ሃዎ አስተዳዳሪ አብዲራሺድ አብዲ “ጥቃቱን የፈጸመው አልሸባብ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የጽጥታ አካላት በቦታው ሲደርሱ ሰባት ሰዎች ተገድለው ማግኘታቸውን የሚናገሩት አስተዳዳሪው “ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ገዳዮቹ የአልሸባብ አሸባሪዎች ናቸው። እስካሁን አልተያዙም። ለምን ስደተኞን ዒላማ አደረጉ ለሚለው ጥያቄ፣ ይህ ግድያ በመላው አገሪቱ ከሚፈጸመው ግድያ የሚለይ አይደለም” በማለት እስላማዊውን ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል።

ስደተኞቹ “ኦሮሞ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ነው እየተካሄደ ያለው” ሲሉ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ መንግስት ታህሳስ 11 የባህር በር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ በቀናት ልዩነት ነበር በሶማሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማስፈራሪያ እና ጉዳት መስተናገድ የጀመሩት።

በሶማሊያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ በቻ ሳይሆን በሶማሊ ላንድ የሚገኙ ዜጎች ላይም ጉዳት እየደረሰ መሆኑ ተዘግቧል። ስምምነቱ ከተፈጸመ ሶስት ቀን በኋላ በሶማሊ ላንድ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የአካል ጉዳት፣ የንብርት መዘረፍ እና የቤት ማቃጠል መኩራ እንደተደረገባቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። 

“ስምምነቱ ከመፈጸሙ በፊት ከሶማሊያ ህዝብ ጋር በሰላም እየኖርን ነበር” የሚሉት ስደተኞቹ፤ ከስምምነቱ በኋላ ግን “ባህራችንን ለመውስደ እየጣረ ያለው የኦሮሞ መንግስት ነው በሚል በኢትዮጵያውያን ላይ በተለይ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የተቀናጅ ዘመቻ እየተካሄደ ነው” ሲሉ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

በሶማሊያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውን ላይ ግድያ ሲፈጸም የእሁዱ ክስተት የመጀመሪያው አይደለም። ጥር 19/ 2016 ጁባላንድ በሚባል አካባቢ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ላይ ግድያ መፈጸሙንና በሌሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድርግ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል። 

ይህን ተከትሎ ነዋሪዎቹ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በደብዳቤ ጠይቀው የተደረገላቸው ጥበቃ ባለመኖሩ በታላቅ ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

አዲስ ስታንዳርድ በሶማሊያ እና ሶማሊ ላንድ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ጉዳይ በተመለከት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ጽ/ቤትን በጽሑፍ አነጋግሯል። ጽ/ቤቱ ለአዲስ ስታንዳርድ በሰጠው ምላሽ፤ በኢትዮጵያወያን ላይ እየተፈጸመ ነው ስለተባለው ጉዳይ ከስደተኞቹ ተወካዮች መረጃ እንደደረሰው በመግልጽ ነገር ግን “ጥቃት ተፈጸሞባቸዋል  ወደተባሉት አካባቢዎች መደረስ ባለምቻሉ መረጋገጥ አለቻልኩም” ሲል ገልጿል። 

ይሁን እንጂ ድርጅቱ ያለውን ስጋት ለብሔራዊ ስደተኞች ኤጀንሲ በማንሳት ስደተኞቹ ለአደጋ በተጋለጡበት አካባቢዎች ተጨማሪ የጸጥታ ሠራተኞች አንዲሰማሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ጠቅሷል። ከዚ በተጨማሪም ከመንግስት አካላት ጋር በመሆን የስደተኞቹን ድህንነት ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን ገልጿል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button