ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ አልሸባብ “ጅግጅጋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች” ለመፈጸም አስቦት የነበረውን የሽብር ጥቃት አከሸፍኩ ሲል መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9/2016 .ም፡ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች “የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 14 የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላት” በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ።

የሽብር ቡድኑ አባላትን በህቡእ በመመልመልና በማደራጀት በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ እና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዕቅድ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ መሞከሩን ግብረ- ኃይሉ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አመላክቷል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የሽብር ቡድኑ አባላት ሊጠቀሙባቸው ካዘጋጇቸው “ተቀጣጣይ ቁሶችና የተለያዩ ሰነዶች” ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አትቷል።

በህግ ቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል “አሊ አብዲ በቅፅል ስሙ መዓሊን አሊ” በመባል የሚታወቀው የሽብር ቡድኑ መሪና አስተባባሪ በሞያሌ ከተማ የመግቢያ ኬላ በኩል ሾልኮ ለመውጣት ሲሞክር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የጋራ ግብረ- ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡

አልሸባብ የሽብር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ ስምሪት የሰጠው “በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ፊቅ፣ ዋርዴር እና ቢኬ” አካባቢዎች እንደነበር ያመለከተው መግለጫው የህቡዕ አደረጃጀት በመፍጠር የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም የተንቀሳቀሱት ተጠርጣሪዎች ለሽብር ጥቃቶች ሊጠቀሙባቸው ካዘጋጇቸው “በርካታ ክላሽንኮቭ መሳሪያዎች፣ ጥይቶች ፣ሽጉጦች፣ ቦንቦች፣ ተቀጣጣይ ቁሶችና” የተለያዩ ሰነዶች ጋር መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ለጥቃት ሊያውሏቸው የነበሩ 84 ክላሽንኮቭ መሣሪያዎች፣ 10 የቡድን መሣሪያዎችና 12 ሽጉጦች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን መግለጫው አክሎ ገልጿል።

ቡድኑ የፈንጅ መቀመሚያ ንጥረ ነገሮች በህቡዕ ባደራጃቸው ህዋሶች አማካኝነት በህገ ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ ድንበር ወደ ደቡብ ሶማሊያ በሟጓጓዝ ላይ እያለ “በኤረር ዞን ጋሻሞ ወረዳ” በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ባወጣው መግለጫ አያይዞ ጠቁሟል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button