ዜናማህበራዊ ጉዳይህግ እና ፍትህ

ዜና፡ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መቋረጥ በቀጠለበት ሀዲያ ዞን መምህራን ለእስር እና ማስፈራሪያ ተዳርገዋል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15/2016 ዓ/ም፡_ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን የሚገኙ መምህራን የወርሃዊ ደመወዝ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው በመጠየቃቸው ለእስር እና ማስፈራሪያ መዳረቻቸውን አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ምንጮች ገለጹ። ደመወዝ እንዲከፈላቸው እየጠየቁ ያሉ መምህራን በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ዒላማ መደረጋቸውና በሚደረሳቸው ማስፈራሪያ ጥያቄያቸውን እንዳያሰሙ መደረጋቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ “የሁለት ወራት ግማሽ ደመወዛቸው ቢፈጸምም፣ በክልሉ ያሉ መምህራንና የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መቋረጥ ችግር አሁንም እንደቀጠለ ነው” ብለዋል። ደመወዝ እንዲከፈላቸው የሚጠይቁ ሰራተኞች በጸጥታ አካላት ለእስር እና ማስፈራሪያ እንደሚዳረጉም ነዋሪው አክለው ገልጿል።

የደመወዝ መዘግየት ችግር በተለይ በሀዲያ ዞን በምስራቅ እና በምዕራብ ባድዋቾ ወረዳ በገጠር አካባቢዎች ከፍተኛ ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች በርካታ መምህራን ደመወዛቸው በመቋረጡ ሳቢያ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አድርጓል። 

የምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ መምህር እንደገለጹት በተደጋጋሚ ባቀረቡት አቤቱታ የመስከረም እና ጥቅምት ወር ግማሽ ክፍያ ቢፈጸምም የቅርብ ጊዜውን ጨምሮ የቀረው ሙሉ ደመወዛቸው ገና አልተከፈለም። በመምህራኑ ላይ እንግልት እየደረሰ መሆኑን የገለጹት መምህሩ፣ የደመወዝ መቋረጥን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የጠየቁ የ40 መምህራን ደመወዛቸውን በባለስልጣናቱ እንደተከለከሉ ጠቁመዋል። በተጨማሪም፣ በምስራቅ ባድዋቾ በግልጽ ቅሬታቸውን ያሰሙ መምህራን በተደጋጋሚ ለእስር መዳረጋቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለይም አዲሱ የክልል አደረጃጀት ተከትሎ የተለያዩ አስተዳደሮች እና መዋቅሮች መልሶ መቋቋም ወይም ተያያዥ ውሳኔዎች ሂደት ጋር የሚነሱ የደመወዝ መዘግየት እና ያለመከፈል የተመለከቱ አቤቱታዎችን፣ እንዲሁም ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ታህሳስ 13 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው በሃዲያ ዞን ከደመወዝ ጋር የተያያዙ ችግሮች ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሚስተዋል መሆኑን እና ከችግሮቹ መካከልም በየወሩ መጨረሻ ሊከፈል የሚገባው ደመወዝ ከ10 እስከ 20 ቀን እንደሚዘገይ እና በተለያዩ ወቅቶች መከፈል ከነበረበት ሙሉ ደመወዝ 30፣ 50 እና 70 በመቶው ብቻ ሲሰጥ መቆየቱን የሚያጠቃልል ነው ሲል ገልጿል። 

ኢሰመኮ “ችግሩ ተባብሶ በዋናነት ከፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶች እና ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በስተቀር በአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ደመወዝ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ በመቆየቱ ለዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ሰራተኞቹ ገልጸዋል” በሏል። በተጨማሪም ኅብረተሰቡ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አገልግሎት በማቆማቸው ወይም በሙሉ ዐቅም አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው ሕክምና ለማግኘት ወደ አጎራባች ዞኖች ለመሄድ በመገደዳቸው ለእንግልትና ለሕይወት አደጋ መጋለጣቸውን ገልጸዋል ብሏል። መግለጫው በከተማ አስተዳደሩ እና በወረዳዎቹ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን አስታውቋል። 

ኮሚሽኑ የከተማና ወረዳ አስተዳደር ኃላፊዎች በበኩላቸው ችግሩ መኖሩን ገልጸው ከምክንያቶች መካከል የውስጥ (የአካባቢ) ገቢ ማነስ አንዱ መሆኑን አስረድተዋል ነው ያለው። ለሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ የሚውል ገንዘብ የሚገኘው ከፌዴራል መንግሥት ተመድቦ በዞን በኩል የሚመጣ በጀት እና የከተማና የወረዳ አስተዳደሮች ከአካባቢው የሚሰበስቡት ገቢ ተደምሮ እንደሆነና አስተዳደሮቹ ይህን ከውስጥ (ከአካባቢው) መሰብሰብ የሚጠበቅባቸውን ገቢ ለማሟላት ዐቅም ስለሌላቸው ለበጀት እጥረቱ አንዱ መንስዔ እንደሆነ ገልጸዋል ሲል ኢሰመኮ በመግለጫው አካቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሚመጣው በጀት ለሌሎች ጉዳዮች ለምሳሌ ለማዳበሪያ ግዢ መዋሉም ሌላ ምክንያት እንደሆነ ኃላፊዎች ያስረዳሉ። በተለያዩ ወቅቶች የተፈጸሙ እና ያልተጠኑ የሠራተኞች ቅጥሮች መኖራቸውም ሌላኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል ተብሏል።

የሃዲያ ዞን አስተዳደር ኃላፊዎች የሚነሳው የደመወዝ ክፍያ ችግር ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማጣራት አምስት የክትትል ቡድን ተደራጅቶ በ19ኙም የከተማ እና ወረዳ አስተዳደሮች ከጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ መሰማራታቸውን እና ቡድኑ በሚያቀርበው ግኝት መሠረት ዞኑ የማስተካከያ እርምጃዎችን የሚወስድ መሆኑን ገልጸዋል በሏል መግለጫው። 

በሃዲያ ዞን አከባቢዎች ከደመወዝ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ቅሬታ እና ተቃውሞ ባሰሙ ሰዎች ላይ ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ድብደባ እና ለተለያዩ ጊዜያት እስራት ጭምር ደረሶባቸዋል ያለው ኢሰመኮ ሁሉም የክልል መስተዳድሮች ተገቢ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ለሠራተኞች ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ መከፈሉን እና ሰብአዊ መብቶቹ መከበራቸውንና መጠበቃቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል ብሏል። 

ኮሚሽኑ ለጉዳዩ የተሟላ ትኩረት በመስጠትና በተለይም በዚህ መግለጫ እንደተመለከተው ችግሩ በይበልጥ በታየባቸው የክልልና የዞን አስተዳደሮች ልዩ ትኩረት በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ማመቻቸት፣ አገልግሎት ያቋረጡ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ወደ ሥራ መመለሳቸውን ማረጋገጥ እና ለወደፊቱም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከል ይገባል ሲል አሳስቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button