ዜናፖለቲካማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ኢዜማ የአዲስ አበባ አስተዳደር የብሔር ኮታን ለከፍተኛ የስልጣን ምደባ በመስፈርትነት ማስቀመጡን እንደሚያወግዝ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ – ኢዜማ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የመንግስት ሰራተኞችን ብቃት እና ባህሪ ለመመዘን በሚል ከ16 ሺህ በላይ የከተማ አስተደደሩ ሠራተኞች ለፈተና እንደሚቀመጡ መግለጹን ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጠው ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።

በመርህ ደረጃ ፓርቲው ፈተና መሰጠቱን እንደሚያምንበት አስታውቆ የአገልግሎት ጥራትን ለማስፈን የምዘና ጅምሩ የሚበረታታ መሆኑን ገልጿል።

በአንድ መሥርያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ዳይሬክተሮች እና የቡድን መሪዎች ከአንድ ብሔር ከ40 በመቶ በላይ ሊበልጡ እንደማይገባ መገለጹ ዋነኛውና መሠረታዊ የሆነውን ከትምህርት ዝግጅት እና ከሥራ ልምድ የሚመነጩ የችሎታና የብቃት ጉዳይ አሳንሶ እንዳይመለከት ጥብቅ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲል አሳስቧል።

ኢዜማ በሀገሪቱ የሚገኙ ተቋማት ለሁሉም ዜጎች እኩል እድል የሚሰጡ መሆን እንዳለባቸው ይገነዘባል ያለው መግለጫው ነገር ግን የብሔር ኮታን በዚህ ደረጃ ከፍተኛ መስፈርት ተደርጎ መቀመጡ አገልግሎትን ማቀላጠፍም ሆነ ማኅበራዊ ፍትህን ማስፈን የማይችል አሠራር በመሆኑ በጽኑ የሚያወግዘው እና የሚታገለው ተግባር መሆኑን አስታውቋል።

የከተማ መሥተዳደሩ ስለ ፈተናው እና የብሔር ኮታ ምደባን አስመልክቶ ለከተማዋ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል።

ኢዜማ በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለሚደረጉ ምደባዎች በምንም ዓይነት መንገድ የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገ መድልኦ የሚደረግባቸው እንዳይሆኑ፤ አሠራሩም ለሁሉም ዜጎች ግልፅና ችግር በሚፈጥሩ አመራሮች ላይ የማያወላዳ ተጠያቂነት ማስፈን የሚችል እንዲሆን ማድረግ ይገባል ብሎ እንደሚያምን አመላክቷል።  

ሚዲያዎችም ሁኔታውን በትኩረት በመከታተል ለሕዝብ ተገቢውን ሚዛናዊ መረጃ በመስጠት እና ችግር ሲፈጠርም ተከታትሎ በመረጃ በማጋለጥ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሰሩ ጠይቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አጋጥሟል በተባለ የቴክኒክ ችግር ሳቢያ ሳይሰጥ የቀረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ሠራተኞች ፈተና በቀጣይ ቅዳሜ ታህሳስ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ይሰጣል መባሉን መዘገባችን ይታወሳል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button