ዜናህግ እና ፍትህ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ወደ ፍርድ ቤት ከሚቀርቡ ጉዳዮች እልባት የሚያገኙት ከ30 በመቶ በታች መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ በአማካይ በየዓመቱ ወደ ፍርድ ቤት ከሚቀርቡ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ጉዳዮች መካከል እልባት የሚሰጣቸው 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን (29.7 በመቶ) ጉዳዮች ብቻ መሆናቸውን የፌደራል የፍትሕና የሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዪት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት አለመውሰድና በሽምግልና የመጨረስ ሁኔታ መኖሩን በመጠቆም ወደ ፍርድ ቤት የሚመጣው ጉዳይ በጣም አነስተኛ መሆኑን አብራርተዋል ያለው ዘገባው ከ30 በመቶ በታች  ጉዳዮች ብቻ እልባት እንዲያገኙ መደረጉ ብዙ ጉዳዮች ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ከመጠቆም ባለፈ በፍትሕ ሥርዓቱ መዘመንና ተደራሽነት ላይ በሰፊው መሥራት አስፈላጊ መሆናን ያሳያል ማለታቸውን አስታውቋል።

ዋናው ችግር ተቋሙ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በሚችልበት ደረጃ ላይ ያለመሆኑ ነው ያሉት አቶ ደግፌ፤ ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል በቂ ባለሙያ ለመሳብና ለማቆየት አለመቻል፣ የሚጠኑ ጥናቶች በተግባር ላይ ያለመዋል፣ የምርምርና የማሠልጠን አቅም ያለመዳበር፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ያለመሟላት ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል ብሏል።

በተለይም ቴክኖሎጂው የፍትሕ ሥርዓት አሰጣጡን ጥሎ እንዳይሄድና በቴክኖሎጂ ተደግፈው የሚሠሩ ወንጀሎችን በብቃት ለመመርመርና ፍትሕ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል ያለው ዘገባው ይህን ለማሻሻል ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተናበበ ግንኙነት መፈጠሩን ጠቁመው፤ ከሀገር ውጭ ከሚገኙ አቻ ተቋማት ጋርም በተመሳሳይ መልኩ የሚከናወኑ አበረታች ተግባራት መኖራቸውን ገልጸዋል ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button