ዜናጤና

ዜና፡ የጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ከ70 ሚሊየን በላይ ሰዎች የኮቪድ ክትባት ሙሉ ዙር ተከትበዋል አለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24/2016 ዓ.ም፡- የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤናው ዘርፍ የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው ስድስት ወር ዕቅድ አፈፃጸምና በዘርፉ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልቶ ለጋዜጠኞች ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም መግለጫ ሰጥተዋል።

“ባለፉት ስድስት ወራት፣ በአንዳንድ ሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች መካከልም ሆነን፣ በጤናው ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ ነበሩ” ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው እስከ አሁን ድረስ 70,180,665 ሰዎች የኮቪድ ክትባት ሙሉ ዙር ተከትበዋል ማለታቸውን ያስታወቀው የሚኒስቴሩ መረጃ በባለፉት ስድስት ወራ 16,367 የሚደርሱ የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 728 በላብራቶሪ የተረጋገጠ የኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው ጠቁመዋል ብሏል።

በስድስት ወራት ውስጥ በበሽታው ምንም አይነት ሞት አልተመዘገበም ማለታቸውንም አካቷል፡፡

ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚሰሩ የአገልግሎት ሽፋን 100 ፐርሰንት ደርሷል ማለታቸውንም አመላክቷል።

የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋንን 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 72 በመቶ፣ በሰለጠነ ባለሙያ የታገዘ የወሊድ አገልግሎት ያገኙት እናቶች 63 በመቶ፣ የህጻናት ጤናን ከማሻሻል አኳያ ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የፀረ አምስት ክትባት ለሶስተኛ ጊዜ ማግኘት የሚገባቸውን 100 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ በ6 ወራት 90 በመቶ፣ ሀገር አቀፍ የኩፍኝ ክትባት የመጀመሪያውን ዙር 100% ለማድረስ ታቅዶ 84 በመቶ፣ የቲቢ ልየታ 81.2 ከመቶ፣ የኤች አይ ቪ ምክክርና ምርመራ አገልግሎትን 92% ለማድረስ ታቅዶ 75.5 በመቶ፣ ለ14 ሚሊዮን ህፃናት የአንጀት ጥገኛ ትላትል እና ለ7 ሚሊዮን ህጸናት ለቢልሃረዚያ በሽታ መድሃኒት እደላመደረጉን የገለጹት ክቡር ሚኒስቴር ዲኤታው የኮሌራ ወረርሽኝ በታየባቸው አከባቢዎች በ6 ዙር ለ8.4 ሚሊዮን ሰዎች ክትባት መስጠት መቻሉን አብራርተዋል ብሏል፡፡

የድንገተኛ አደጋ፣ ድርቅ እና ግጭት በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የአእምሮ ጤና፣ የስነ-ልቦና፣ ማህበራዊ ድጋፍ፣ የመድኃኒት አቅርቦቶች እና የባለሙያዎች ምደባ ስራዎች በስፋት መሰራታቸውን ገልጸዋል ብሏል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button