ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “የአማራ ክልል መሬቶቼን የራሱ በማድረግ በትምህርት ካሪኩለሙ ማካተቱ ተቀባይነት የለውም” ሲል የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዛሬ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የአማራ ክልል መንግስት “የትግራይ መሬቶችን የግዛቱ አካል በማድረግ” በክልሉ ካርታ ላይ በማስፈር እና በትምህርት ካሪኩለሙ በማካተት እያስተማረበት እንደሚገኝ ተረድቻለሁ ብሏል።

ክልሉ ይህን ያደረገው “ሃላፊነት በጎደለው” መልኩ ብቻ ሳይሆን፤ “ትግራይን ቆራርሶ የማጥፋት ዘመቻ እንዳይቆም እና በከፋ መንገድ አሁንም እየሰራበት ስለመሆኑ ለመገንዘብ ችለናል” ሲል ኮንኗል።

“የአማራ ክልል መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ እየፈጸመው የመጣውን እና በጉልበት በተቆጣጠራቸው የትግራይ አከባቢዎች እየፈጸመው ያለው ግፍ እና መከራ እንዳይበቃ፤ በፈጸማቸው ጥፋቶች ሊጸጸት ሲገባው እንደዚህ አይነቱን ታሪካዊ ስህተት ውስጥ መግባቱ ዋጋ የሚያስከፍለው መሆኑን አውቆ በአፋጣኝ ሊያርመው ይገባል” ብሏል።

የፌደራል መንግስቱም ከዚህ በፊት በፌደራል መንግስቱ ተቋማት፣ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል “ሃላፊነት በጎደለበት አኳኋን” በመዘጋጀት ያሉ ካርታዎች እንዲታረሙ ማድረግ እና አስፈላጊ እርምጃዎችንም መውሰድ ሲገባው “አይቶ እንዳላየ ማለፉ የጥፋቱ አካል መሆኑን የሚያመላክት ነው” የሚሆነው ሲል ገልጿል።

የትግራይ ህዝብ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶርያው ስምምነት በተሟላ መልኩ በመፈጸም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በሙሉ ሃላፊነት እየሰሩ ባለበት ወቅት የአማራ ክልል መንግስት የዚህ አይነት ተግባር መፈጸሙ “የሰላም ሂደቱን ለማደፍረስ ሆን ብሎ የሚፈጽመው ጥፋት መሆኑ” ሊሰመርበት ይገባል ብሏል።

የአማራ ክልል ህዝብም ይሁን ሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች በትግራይ ህዝብ ላይ የአማራ ክልል መንግስት እየተፈጸመ የመጣውን እና አሁንም በመቀጠል ላይ ያለውን “ግፍ እና በደል” ይቁም ብሎ ከትግራይ ህዝብ እና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥሪ ያቀርባል።

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን “ይህን ተከትሎ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው የአማራ ክልል መሆኑን ልናሳውቅ እንወዳለን” ብሏል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button