ዜና

ዜና፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት ባለመሥራቱ ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ ማጣቷን ቋሚ ኮሚቴው አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1/ 2016 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር በዋናነትም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት ባለመሥራቱ ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ ማጣቷን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

በሁለቱ ተቋማት መገፋፋት እና በቅንጅት ባለመሥራታቸው ምክንያት ከ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አለመገኘቱ ተገልጿል። 

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያለው፤ በትላንት መጋቢት 30፣  የ2014/15 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ፕሮጀክት አፈጻጻም የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን በገመገመበት ወቅት ነው። 

የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ፤  ኃይል ሲቋረጥ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መካከል ኃላፊነት ወስዶ ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ በእቅድ ላይ የተመሠረተ ሥራ አለመሰራቱን ተናግረዋል።

ከአገልግሎቱ ጋር በቅንጅት ባለመሥራቱ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ውስጥ እና ለጎረቤት ሀገሮች ባለመሸጡ በአማካኝ አንድ ቢሊዮን 271 ሚሊዮን 244 ሺህ 977 ብር ድርጅቱ ማጣቱን በ2013 ዓመታዊ ሪፖርት የተገለጸ መሆኑ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል ብለዋል።

ሰብሳቢዋ፤ እነዚህ ተቋማት እንደ ሀገር ትልቅ ኃላፊነት የተሰጣቸውና እንደ አንድ የሚታዩ መሆናቸውን ገልጸው፤  ነገር ግን ድርጅቶቹ ምንም አይነት የሕግ ማዕቀፍ በሌለው መንገድ መሥራታቸው ምክንያት ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንዳታገኝ አድርጓል ብለዋል።

በቀጣይ በሕግ የታሠረ በስምምነት ሰነድ የተደገፈ ቅንጅታዊ አሠራር በአስቸኳይ በመመሥረት ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በተለያዩ ጊዜያት በመገናኘት የእቅድም ሆነ የኦፕሬሽን ሥራዎችን በቅንጅት ተወያይቶ ይሠራል ብለዋል።

ነገር ግን ቋሚነት ያለው የተፈረመ ሰነድ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የለም ሲሉ ገልጸው፤ ይህም እንደ ክፍተት የሚወሰድ ይሆናል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው ችግር አሁን ላይ እየተቀረፈ ይገኛል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ችግሩ በሁለቱ ተቋማት መገፋፋት የመጣ አይደለም ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው አስረድተዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

በተጨማሪም ድርጅቱ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እንዲሁም ከክልሎች ጋር በጥሩ ግንኙነት እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በቀጣይ በጀት ዓመት ያሉትን ክፍተቶች በማስተካከልና የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የቅንጅት ሥራውን ለማጠናከር ጥረት ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button