ዜናህግ እና ፍትህ

ዜና፡ በመራዊ የተፈጸመው ግድያ በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት እንዲመረመር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4/2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በመራዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ከፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ በመከላከያ ሠራዊት የተፈጸመው የንጹሃን ገድያ የጦር ወንጀል እና ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ መሆኑ በአስቸኳይ የአፍሪካ እና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ምርመራ እንዲያደርጉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ። 

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ያለውን ምርመራ እንዲጀምርም አሳስቧል። 

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በመራዊ የተፈጸመውን የሲቪሎች ግድያ በተመለከተ ከሳታላይት ምስል ጋር አያይዞ ዛሬ ሚያዚያ 4/ 2016 ባወጣው ሪፖርት፤  ጥር 21 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች የአከባቢውን ሰዎች ከቤታቸው፣ ከሱቆቻቸው እና ከጎዳናዎች ላይ ሰብስበው በርካታ ሰዎችን በጥይት መግደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውኛል ሲል ገልጿል።

በጥቃቱም ከ50 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ሟቾቹን ከቀበሩ አራት ሰዎች እና ከአንድ ባለስልጣን መስማቱን በመግለጫው አክሏል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጠናዊ ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ፤ “በኢትዮጵያ የጅምላ ግድያ በአስደንጋጭ ሁኔታ የተለመደ እየሆነ ምጥቷል” ሲሉ ገልጸው፤ “ባለፈው አመት የተባበሩት መንግስታት መርማሪዎች ከ2020 ጀምሮ በትግራይ ብቻ ከ48 በላይ “ትላልቅ” ግድያዎች መፈጸማቸውን ሪፖርት አድርገዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ለሟች ቤተሰቦች ፍትህን ለማረጋገጥ እና ይህን መሰል ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት የለም ” ሲሉ ተናግረዋል። 

አምነስቲ አራት የተጎጂ ዘመዶችን እና አምስት ከመንገድ ላይ አስክሬ ያነሱ እንዲሁም የማህበረሰብ መሪዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 13  ግለሰቦችን አናግሮ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ የመጀመሪያውን ግኝቶቹን ለኢትዮጵያ መንግስት ማጋራቱን እና እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መቶች ከሚሽን በወቅቱ ባወጣው መግለጫ በመራዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂ  ኃይሎች መካከል ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ፣ ማንነታቸው ማረጋገጥ የተቻለ ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል ብሏል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም ሂዩማን ራይት ዎች መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል “የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል” ሲል ከሷል። በመራዊ የተፈጸመውን ግድያ በማሳያነት ያቀረበው ተቋሙ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል የተፈጸመውን የንጹሃን ግድያ በተመለከተ ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቋል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በመራዊ ጥር 20 በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ግጭት እንደነበር አርጋግጠው “ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ ርምጃ በመንግሥት ኃይሎች አልተፈጸመም” ሲሉ ውንጀላውን አስተባብለዋል፡፡

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቃለ መጠይቅ የተደረገባቸው የመራዊ ከተማ ነዋሪዎች፤  የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ቤት ለቤት እየሄዱ እና የቀን ሰራተኞች የሚመገቡበት ቁርስ ቤት በመሄድ ግድያ ፈጽመዋል ብለዋል። 

አሚነስቲ በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ ቪዲዮ ላይ ምርመራ በማድረግ በዋና መንገድ ላይ ቢያንስ  የ22 ሰዎች አስክሬን መታየቱን መረጋገጡን ገልጿል። ድርጅቱ በመግለጫው የአመታዊው ቅደት ማርያም በዓል ለማክበር ወደ መራዊ ያመራ አንድ አይን እማኝ ወታደሮች መንገድ ላይ በርካታ ነዋሪዎች ላይ ሲተኩሱ ማየቱን ተናግሯል ብሏል።  

ከጥበቃ ሰራቸው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ የነበሩ የ70 አመት አዛውንትም በመከላከያ ሠራዊት መገደላቸውን ድርጅቱ በሪፖርቱ አካቶ ገልጿል።

ኪዚህ በተጨማሪም የመከላከያ ሰራዊት ኃይሎቹ  የባጃጃ ተሽከርካሪዎችን እና አንድ ሞተር ሳይክል ማቃጠላቸውም  የአይን እማኞች እና ሶስት ንብረቱ የወደመባቸው ሰዎች ተናግረዋል።  አምነስቲ የሳተላይት ምስልን በመጠቀም አስክሬኖች በሚታዩበት በከተማዋ መንገዶች ላይ ቢያንስ አምስት ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል። 

የሰብዓዊ መብት ተቋሙ፤ ከዚህ ቀደም ለተፈፀሙ ወንጀሎች ፍትህ እንዲረጋገጥ እና እየተካሄዱ ያሉት ሁከቶች እንዲቋጩ በሕይወት የተረፉና የተጎጂ ቤተሰቦች ጭምር ቢጠይቁም የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ለማድረግ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ተግባር አልወሰደም ሲል መንግስትን ከሷል።

“የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት መረጋገጡን መናገሩ ለእውነተኛ ፍትህ እና ተጠያቂነት የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖሩን ያሳያል” ሲሉ ቲጌሬ ቻጉታህ ገልጸዋል። 

ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችሉ ብሔራዊ ጥረቶች ባለመኖራቸው በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ምክንያት ሆኗል ብሏል አምነስቲ። 

አምነስቲ እንተርናሽናል የተባበሩት መንግስታት ድርግት ልዩ ራፖርተር ከህግ ውጭ እና በዘፈቀደ የተፈጸሙ ግድያዎችን እና የአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ወንጀሉን እንዲመረመሩ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ለተቋማቱ የጉብኝት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ጥሪ አቅርቧል። 

“ኢትዮጵያውያን ከዚህ በላይ ፍትህን መጠበቅ አይችሉም። በአማራ ክልል የመብት ጥሰቶች በመቀጠላቸውና በአገር አቀፍ ደረጃ ፍትህን ለማስፈን ቁርጠኝነት ባለመኖሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ምርመራውን ወደነበረበት ለመመለስ እርምጃ መውሰድ አለባቸው” ሲሉ ቲጌሬ ቻጉታህ አሳስበዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button