ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ኢትዮጵያ የኪሳራ ማካካሻ ሀሳብ በማቅረብ ከቦንድ አበዳሪዎቿ ጋር ለመደራደር ማቀዷ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5/2016 .ም፡ ኢትዮጵያ ከቦንድ አበዳሪዎቿ ጋር ትላንት ሐሙስ ታህሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት በቨርቹዋል ባደረገችው ውይይት የቦንድ አበዳሪዎች ለሚያጋጥማቸው ኪሳራ ማካካሻ የሚሆን ውል ለማቅረብ ማቀዷን ገልጻለች ተባለ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በገንዘብ ሚኒስቴር ባለስልጣናት እና በቦንድ አበዳሪዎች መካከል በተካሄደው ውይይት ወቅት ተሳታፊ ከነበሩ ሶስት ሰዎች ሰማሁ ብሎ ባቀረበው ዘገባ የኢትዮጵያ መንግስት ለአበዳሪዎቹ አዲስ ውል ማዘጋጀቱን እና በውሉም አበዳሪዎቹ የሚያጋጥማቸውን ኪሳራ የሚያካክስ ሀሳብ ማካተቷን አስታውቋል ብሏል።

ኢትዮጵያ ትላንት በተካሄደው ውይይት ለአበዳሪዎቿ ያቀረበችው የመፍትሄ ሀሳብ ባሳለፍነው ሳምንት ለዋና ዋና የቦንድ ገዢዎች ቡድን አቅርባ ውድቅ ከተደረገባት ሀሳብ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ውይይቱን ከተካፈሉ ሰዎች መስማቱን ሮይተርስ ጠቁሟል።

ኢትዮጵያ በመፍትሄ ሀሳብነተ ያቀረበችው በድጋሚ ብድሯን መመልስ የሚያቅታት ከሆነ አበዳሪዎቹ እንዳይጎዱ የሚያደርግ ማካካሻ ያካተተ መሆኑን ምንጮቹ እንደገለጹለት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኛ ስጋት ለዩሮ ቦንዱ አበዳሪዎቹ ወለዱን ከከፈለ ዋነኛ አበዳሪዎቹ እነ ቻይና ጥያቄ እንዳያስነሱበት መሆኑን የዜና አውታሩ በዘገባው አመላክቷል።

ኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ ገዢዎች የእዳ ክፍያውን ሌሎች አበዳሪ አገራት ከሰጧት ጊዜያዊ የእዳ መክፈያ ጊዜ የማራዘም ውሳኔ ጋር እንዲያጣጥሙላት መጠየቋንም ዘገባው አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ገበያ የሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ አከፋፈል ላይ ከአበዳሪዎቿ ጋር ያደረገችው ድርድር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የውጭ ዕዳዋን መክፈል የማትችልበት ደረጃ (ዲፎልት) ላይ ለመድረስ ጫፍ ላይ ትገኛለች ሲል ሮይተርስን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢትዮጵያን የቦንድ ግዢዋን ከፈጸሙ ዋና ዋና ተቋማት ጋር ያደረገችው ድርድር ህዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ያለውጤት ተጠናቋል ያለው ሮይተርስ በአንድ ወቅት ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ተስፋ ተጥሎባት የነበረች ሀገር አሁን ብድሯን መክፈል ተስኗታል ሲል መግለጹም ተካቷል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button