ዜናፖለቲካማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአዲስ አበባ ለመንግስት ሰራተኞች ሊሰጥ የነበረው ፈተና ላልታወቀ ግዜ ተራዘመ፣ የአዲስ አበባ እና የኮተቤ ዩኒቨርሲቲዎች ለመራዘሙ ምክንያት መሆናቸው ተገልጿል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12/2016 .ም፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞችን ብቃት እና ባህሪ ለመመዘን በሚል ከ16 ሺህ በላይ የከተማ አስተደደሩ ሠራተኞች ትላንት አርብ ታህሳስ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ለፈተና እንደሚቀመጡ ቢገለጽም ፈተናው ሳይሰጥ ቀረ። አስተዳደሩ ፈተናው ያልተሰጠው ባጋጠመ የቴክኒክ ችግር ነው ብሏል።

አጋጠመ የተባለው የቴክኒክ ችግር የተፈጠረው የከተማ አስተዳደሩ የምዘና ስራውን እንዲያከናውኑ ሀላፊነት በሰጣቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መሆኑም ተገልጿል።

ሁለቱ የትምህርት ተቋማት ከአስተዳደሩ ጋር ስምምነት በመፈጸም ወደ ስራ መግባታቸውን የገለጸው የከተማ አስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ በስምምነቱ መሰረት የከተማ አስተዳደሩ የሰው ኃይል የማቅረብ፣ መረጃን የማሟላት ኃላፊነቱን የሚወጣ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎቹ በበኩላቸው ፈተናውን የማዘጋጀት፣ ፈታኝ የማዘጋጀት፣ የፈተና ቦታ የማዘጋጀት ፣ መፈተንና ውጤቱን ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነቶች መውሰዳቸውን ጠቁሟል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ገልለተኛ የባለሞያዎች ቡድንን በማቋቋም የክህሎትም የባህሪም ፈተናዎቹን በጥራት እና በከፍተኛ ጥንቃቄ አዘጋጅተው ለመፈተን ዝግጁ አድረገው መቆየታቸውን የዩኒቨርስቲው ሀላፊዎች ገልጸዋል።

ነገር ግን በመጨረሻው ሰዓት ባጋጠመ የቴክኒክ ችግሮች ፈተናው ወደ ሌላ ግዜ እንዲሸጋገር ማድረጋቸውን አመላክተዋል። ፡

አጋጠመ የተባለው ዋነኛ የቴክኒክ ችግሮች ተፈታኞች ስማቸውን ጽፈው ሳይሆን በኮድ የሚፈተኑ በመሆኑ በኮድ አሰጣጥ ላይ ያጋጠመ ችግር መሆኑን የሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች መናገራቸውን የአስተዳደሩ መረጃ ያሳያል።

ችግሮቹን ባለው አጭር ግዜ ለማስተካከል አዳጋች በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለከተማ አስተዳደሩ ፈተናው ለሌላ ግዜ እንዲሸጋገር ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የከተማ አስተዳደሩ ፈተናው በዚህ መልክ መሰጠቱ ፍትሃዊነቱን እና ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰጥ ለማስቻል ጥያቄውን ተቀብሎ ፈተናው ለሌላ ቀን እንዲሸጋገር መፈቀዱንም ተናግረዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ዩኒቨርሲቲዎቹ ለተፈጠረው ችግር የከተማ አስተዳደሩንም ሆነ ተፈታኞችን ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን የቴክኒክ ችግሮቹ በአጭር ግዜ ተፈተው እና አዲስ መርሃ ግብር ወጥቶ ፈተናው እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡

ፈተናው ምንም አይነት የደህንነት ችግር የሌለበት ሲሆን በአስተማማኝ ጥንቃቄ መቀመጡንም አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ሚስጥራዊነቱ እና ፍትሃዊነቱ ተረጋግጦ ፈተናው በአጭር ግዜ ውስጥ እንደሚሰጥና ለዚህም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል።

ፈተናውም በሶስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ እንደሚሰጥ መዘገባችን ይታወሳል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button