ዜናማህበራዊ ጉዳይህግ እና ፍትህ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያዊውን በማገት ማስለቀቂያ ገንዘብ የጠየቁ ሁለት ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4/2016 ዓ.ም፡- በደቡብ አፍሪካ በምትገኘው ሊምፖፖ አውራጃ የሚኖሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን አንድ የሀገራቸው ተወላጅ የሆነን የ20 አመት ወጣት ኢትዮጵያዊ በማገት ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቃቸውን እና በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአውራጃዋ ፖሊስ ማስታወቁን አይኦኤል በድረገጹ አስነብቧል።

የ20 አመት ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም መታገቱን የተመለከተ ሪፖርት ፖሊስ እንደደረሰው እና ወዲያውኑ ምርመራ መጀመሩን ያስታወቁት የአውራጃው የፖሊስ ቃል አቀባይ ማሌሴላ ሌደዋባ ወጣቱን ለማስለቀቅ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን 80ሺ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ማስለቀቂያ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል። አጋቾቹ ኢትዮጵያውያን የ20 እና 22 አመት ወጣቶች መሆናቸውን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።

ወጣቱን ለማስለቀቅ በተደረገ ኦፕሬሽን ሌሎች ስምንት ኢትዮጵያውያንም አብረው በአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ መያዛቸውን እና ታግተው ሳይሆን እንዳልቀረ ዘገባው አመላክቷል። በሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ ፖሊስ ምንም አይነት መረጃ አለመስጠቱን ያካተተው መረጃው በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ሳይሆን እንዳልቀረ ጠቁሟል። ታጋቾቹን ሲጠብቁ እና ሲመግቡ የነበሩ ሁለት ሌሎች ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘገባው አካቷል።

በእገታ ውስጥ ከነበሩት መካከል አንዱ ከታገተ ሶስት ወር ያለፈው በመሆኑ ለህክምና ወደ አከባቢው ሆስፒታል መወሰዱን የጠቆመው ዘገባው ሌሎቹ ከ10 እስከ 15 ቀን እንደሆናቸው አመላክቷል። ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የተከፈለ ምንም ገንዘብ አለመኖሩን ድረገጹ በዘገባው አመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button