ማህበራዊ ጉዳይዜና ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና ትንታኔ: በትግራይ የመማር ማስተማር ስራው ቢጀምርም ያልተቀረፉ ችግሮች መኖራቸውን የትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊዎች ገለፁ

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 22/2015 ዓ.ም:- በትግራይ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ለሶስት አመታት ተቋጦ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ስራ የፕሪቶሪያው ስምምነት ባስገኘው ሰላም ዳግም ተጀምሯል።

ምንም እንኳ የመማር ማስተማር ስራው ቢጀምርም  ያልተቀረፉ ችግሮች መኖራቸውን የትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡

በራያ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጀ ዲን ረዳት ፕሮፌሰረ መብራህቶም ጉኡሽ ጦርነቱ ካደረሰው የማተሪያል ውድመት በላይ ወደ ዩኒቨርስቲው የመጡ “ተማሪዎች ሰነልቦና” አስጨናቂ መሆኑን እና ነገሮችን ከባድ ማድረጉን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል። ወደ ትምህርት ገበታ ከተመለሱ ተማሪዎች መካከል ቤተሰቦቻቸውን ያጡ፣ ንብረታቸውን በጦርነቱ ካጡ ቤተሰቦች የመጡ፣ ምንም የሚማሩበት ገቢ የሌላቸው በርካቶች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ ኮፒ ማድረጊያም ሆነ ፕሪንት አድርገው ለማንበብ የሚያስችል ገንዘብ የላቸውም ሲሉ አክለው ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲው በቻለው መጠን ኮፒ እና ፕሪንት በማድረግ ለመተባበር እየጣረ መሆንን የገለፁት ዲኑ “ ከአቅማችን በላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ ተፅእኖ ውስጥ መቆየታቸው አስቸጋሪ ሁኔታን መፍጠሩን የገለፁት ረ/ፕሮፌሰሩ  አክለው፣ እንደበፊቱ ጥናትን መሰረት ያደረገ ትምህርት መስጠት ባንችልም ቢያንስ የተወሰነ ይዘው መውጣት ያለባቸውን ትምህርት እንዲያገኙ እያደረግን ነው ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በትግራይ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች መካከል በቅድሚያ ድጋፍ እንዲደረግለት የጠየቀው አክሱም ዩኒቨርስቲ ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምንም አይነት ማቴሪያል ሳይኖር ትምህርት መጀመር እንቅፋት አይሆንም ወይ ስንል የጠየቅናቸው የዪኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በሰጡን ምላሽ ከተማሪዎቻችን ጋር በነበረን ምክክር ችግር እንደለ ተግባብተናል ሲሉ ገልጸው ያለውን ችግር ከግምት ውስጥ አስገብተው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ተነጋግረናል ብለዋል። በአጠቃላይ ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ጋር የተወያየነው ዩኒቨርስቲው ባለው አቅም የተማሪዎቹን ትምህርት ለማስቀጠል ነው፤ ክፍተት እንኳ ቢታይ ክፍተቱን ችለህ ማለፍ ነው፣ በዚህ ደረጃ ነው የተስማማነው ሲሉ አብራርተዋል።

የአዲግራት ዩኒቨርስቲ የሬጅስትራት ጽ/ቤት ሃላፊ ገብረመስቀል በርኸ በበኩላቸው በርካታ የዩኒቨርስቲው ንብረት መዘረፉን፣ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ህንጻዎች መኖራቸውን፣ መጠገን የሚችሉትን እንደ ወንበር እና ጠረንጴዛዎችን በመምህራን የመጠገን ጥረቶች እየተገረጉ መሆንን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀው ገልፀዋል፡፡

አላቂ ነገሮች እየተገዙ በመሟላት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው የመማር ማስተማሩን ሂደት በራስ አቅም እራሳችንን አደራጅተን አስጀምረናል ብለዋል።

የአዲግራት ዩኒቨርስቲ የሬጅስትራት ጽ/ቤት ኃላፊው ገብረመስቀል በባጀት ደረጃ ስለተለቀቀልን በርካታ መሟላት ያለባቸውን ግብአቶች በማሟላት ላይ እንገኛለን፤ ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት አድርገናል ብለዋል። ኃላፊው የተማሪዎችን መኖሪያ መዘጋጀቱን፣ መገዛት ያለባቸውን በተከቀቀልን ባጀት መሰረት ገዝተን አሟልተናል ብለዋል። በዋናነት ግን የዩኒቨርስቲው ካውንስል ሁለት ግዜ ተሰብስቦ መማር ማስተማረየን ሂደት ማስጀመር እንችላለን ብሎ መወሰኑን አመላክተዋል።

የትምህርት መማር ማስተማር የጅማሬ ሂደቱ ምን ይመስላል ስንል የጠየቅናቸው የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት ስንናፍቀው የነበረው ነው፣ ምንም ይሁን መጀመሩ እራሱ ትልቅ ተስፋ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር የኤርትራ ወታደሮች ከአንዳንድ አካባቢዎች በለመውጣታቸው ስጋት ሆነውብኛል ሲል መግለፁን በማስታወስ ትምህርት የተጀመረው በቂ የጸጥታ ሁኔታ በመፈጠሩ ነው ወይ ስንል የጠየቅናቸው አቶ ገ/መስቀል በፌደራሉ የትምህርት ሚኒስቴር እና በአዲግራት ዩኒቨርስቲ አመራሮች ውይይት ተገምግሞ አዎ መባሉን ገልጸዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊዎች ወደ ክልሉ በመምጣት በመቀሌ ውይይት ማካሄዳቸውን አቶ ገ/መስቀል አስታውቀዋል።

በራያ ዩኒቨርስቲ በኩል የጸጥታ ስጋት አለ ወይ ስንል የጠየቅናቸው ረዳት ፕሮፌሰር መብራህቶም ግኡሽ  ራያ ዩኒቨርስቲ በአማራ ክልል በኩል ከሚገኘው ከትግራይ ወሰን ራቅ ያለ ማለትም ከአላማጣ እና ኮረም ራቅ ስለሚል የጸጥታ ስጋት የለውም ብለዋል። ከወቅቱ ሁኔታም ጋር ተያይዞ ጠበቅ ያለ የጸጥታ መዋቅር እና ጥበቃ ስለሚደረግለት፣ ከከተማው ጋርም የተቀናጀ የጸጥታ ስራ ስለሚሰራ ችግር የለም፣ የመማረ ማስተማር ሂደቱ በስነስርአት እየሄደ ነው ብለዋል። 

ከተማሪዎች ቅበላ ጋር ተያያዞ የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የሆኑትን ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ ይመጣሉ ብለን ከጠበቅናቸው ተማሪዎች ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት መጥተዋል ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። የትምህርት ሚኒስቴር አመቻችቶት በነበረው የመማር እድል ተጠቃሚ ያልነበሩ፣ ትምህርታቸውን ያልተከታተሉ መጥተዋል ሲሉ የገለጹልን ፕሬዝዳንቱ በርካቶቹ ግን በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን ተከታትለው ነገር ግን ያልጨረሱ ናቸው ብለዋል።

በራያ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጀ ዲን ረዳት ፕሮፌሰሩ መብራህቶም ጉኡሽ በበኩላቸው እስከ 1300 ተማሪዎች ይገባሉ ተብሎ ተጠብቆ የገቡት 900 የሚደርሱ ተማሪዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በትግራይ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው ሲማሩ የነበሩ እና በጦርነቱ ሳቢያ በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን የቀጠሉ ተማሪዎች የተሟላ ዶክመንት የላቸውም። በዚህ ጉዳይ ምን እየተደረገ ነው ስንል የጠየቅናቸው የአዲግራት ዩኒቨርስቲ የሬጅስትራት ጽ/ቤት ሃላፊ ገብረመስቀል በርኸ በሰጡን ምላሽ ከትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠን መመሪያ እንደሚያመላክተው እርስ በርስ ዩኒቨርስቲዎች ዶክመንቱን ተቀያየሩ የሚል ነው ብለዋል።

እኛጋ ያሉ ዶክመንቶችን ለሚማሩበት ዩኒቨርስቲዎች እንድንልክ፣ ወደ እኛ የሚመጡ ተማሪዎችን ደግሞ ትምህርታቸውን ሲከታተሉበት ከነበረው ዩኒቨርስቲዎች ዶክመንቶቻቸውን እንድንቀበል ተነግሮናል ብለዋል። በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የተከታተሉት ትምህርት ትንሽ ከሆነ ወደ እኛ ህጋዊ ዶክመንታቸው ተልኮልን ከእኛ ጋር እንዲጨርሱ ይደረጋል መባሉን ነግረውናል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ሲማሩ የነበሩትን ነው አሁን እያስተማርን ያለነው ሲሉ የገለጹልን በራያ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰረ መብራህቶም ጉኡሽ ትምህርታቸውን በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ሲከታተሉ የነበሩ የእኛ ተማሪዎችን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተስማማነው ዶክመንቶቻቸውን ወደ እኛ ልከውልን እኛ ማስረጃዎቹን እንድናዘጋጅ ነው ብለዋል። አብዘሃኛውን ትምህርታቸውን በሌላ ዩኒቨርስቲ የተከታተሉትን ደግሞ እኛ ለየዩኒቨርስቲዎቻቸው እንልክላቸዋለን፤ በዚህ መልኩ የተማሪዎቹን ዶክመንት የምንለዋወጠው ሲሉ ገልጸዋል።

የመምህራን ሁኔታን በተመለከተ በተያዘው ክረምት መግቢያ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት በጦርነቱ ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው ይሰሩ የነበሩ የትግራይ ዩኒቨርስቲዎች መምህራን እንዲመለሱ ማሳሳቡን ተከትሎ አብዛኛዎቹ መምህራቻችን ወደ ዩኒቨርስቲዎቹ መጥተዋል ሲሉ የአዲግራት ዩኒቨርስቲ የሬጅስትራት ጽ/ቤት ሃላፊ ገብረመስቀል ገልጸውልናል።

ረዳት ፕሮፌሰረ መብራህቶም ጉኡሽ በበኩላቸውአዎ አብዘሃኛው ተመልሰዋል ሲሉ ገልጸው “በጦርነቱ የተጎዱ፣ የሞቱም አሉ፤ በጦርነቱ ሳቢያ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎቸ የመቀጠር እድል አግኝተው አማራጩን በመጠቀም በዚያው የቀሩም አሉ” በማለት ተናግረዋል፡፡

የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገብረእየሱስን አንዳንድ መምህራን በተመደቡበት ዩኒቨርስቲዎች የጀመሩት ኮርስ ስላለ እሱን እስኪ ጨርሱ ለአንድ ወር ግዜ እንድንሰጣቸው ከጠየቁት በስተቀር ሌሎቹ ተመልሰዋል ብለዋል።  አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button