ጤናትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ትንታኔ፡ የፈውስ አልባ መድኃኒቶች ስርጭት፤ ደረጃቸውን ያልጠበቁ እና በህገወጥ መንገድ ወደ ገበያ የሚቀርቡ መድኃኒቶች ስርጭት መስፋፋት በኢትዮጵያ 

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6/2016 ዓ/ም፦ ደረጃቸውን ያልጠበቁ እና በህገወጥ መንገድ ወደ ገበያ የሚቀርቡ የመድኃኒት ምርቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ዋነኛ ስጋት ተደርጎ ከተቆጠረ አመታትን አስቆጥሯል። አሉታዊ ተጽዕኗቸው ባለደጉ ሀገራት እጅግ የከፋ መሆኑ የተገለጸው ህገወጥ የመድሃኒት ዝውውር በየአመቱ አንድ ትሪሊየን ዶላር የሚጠጋ ግብይት ይካሄድበታል ሲል የአለም የጤና ድርጅት ከሁለት አመታት በፊት ባወጣው ሪፖርት ጠቁሟል። በአለም አቀፍ ደረጃ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ቀጥሎም ትልቅ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት መሆኑም ይነገራል።

ደረጃቸውን ባልጠበቁ እና በህገወጥ መንገድ ወደ ገበያ በሚቀርቡ መድኃኒቶች ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በየአመቱ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጋ ሰው እንደሚሞቱ የአለም የጤና ድርጅት የቅርብ ግዜ ጥናት ሪፖርት ያመላክታል።  

እነዚህ ከደረጃቸው በታች የሆኑ መድኃኒቶች ፈውስ አልባ መሆናቸውና የሚነገርላቸው መድኃኒቶች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት በስፋት ለሽያጭ የሚቀርቡት በኮንትሮባንድ መሆኑ እና በሀገሪቱ በመበራከት ላይ እንደሚገኝ የህክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል። 

በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በሌሎች ምክንያቶች በኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ የገቡ በቂ የመድኃኒት አቅርቦት ማግኘት አዳጋች እየሆነ መምጣቱ፤ ለሕገወጥ መድኃኒት ዝውውር መስፋፋት እና ደርጃቸውን ያለጠበቁ መድኃኒቶች በመድኃኒት መደብሮች እንዲገኙ ሰበብ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። 

በርካታ ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶች በሀገራችን በመበራከት ላይ ይገኛሉ፤  ከነዚህ መካክል አንዱ ከጉበት ህመም ጋር ተያይዞ ፕሮቲን በጣም ሲያንስ እሱን ለመተካትና ጉበት ላይ የሚከሰተው እብጠት እንዲጠፋ የሚሰጠው “አልቦሚን” የተሰኘው መድኃኒት ነው_ ዶ/ር መሃሪ ( ስማቸው የተቀየረ)

በአዲስ አበባ ተ/ሃይማኖት አከባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው፤ በገበያ ላይ የሚገኝ በ90 ሺህ ብር የገዙት መድኃኒት ደረጃውን ያልጠበቀና እንደማይሰራ ያወቁት ዶክተሮችቹ እጅ ሲድርስ ነበር።

በጉበት ህመም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ እናታቸውን ሲያስታምሙ እንደነበር የገለጹለት አቶ ጌታቸው በህክምና ዶክተር የታዘዘላቸውን `አልቦሚ`(Albumine) የተሰኘ መድሃኒት ገዝተው ለዶክተሩ ቢሰጡትም መድኃኒቱ ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ እንደማይጠቀሙት እንደተነገራቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ዶክተሩ፤ “ይሄንን ብራንድ መድሃኒት ከዚህ በፊት ተጠቅሜበት እጀ ሰባራ አድርጎኛል፤ ደረጃውን ያልጠበቀ እና ምንም ፈውስ የማይሰጥ በመሆኑ እናትህ በጽኑ ታመው ባሉበት ሁኔታ ይህን መድኃኒት አልጠቀምበትም” ሲሉ ገልጸውልኛል ብለዋል።

በዶክተሩ ትዕዛዝ 90 ሺ ብር የገዙትን መድኃኒት ትተው ከሶስት ቀናት በኋላ ከዱባይ ሌላ መድኃኒት ከማስመጣጣታች ከሰአታት በፊት የእናቱ ህይወት ማለፉን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

የውጨ ምንዛሬ እጥረት ይበልጥ በኮንትሮባንድ ለሚገቡ የመድኃኒት ምርቶች ሀገሪቱን ተጋላጭ አድርጓታል _ ዶ/ር መሃሪ

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ክሊኒክ የአንዱ ዋና ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር መሃሪ ( ስማቸው የተቀየረ) ፤ በየጊዜው ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶች የወሰዱ ታካሚዎች ለከፋ አደጋ እየተጋለጡ ነው ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

በርካታ ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶች በሀገራችን በመበራከት ላይ ይገኛል ያሉት ዶ/ር መሃሪ፤  ከነዚህ መካከል አንዱ ከጉበት ህመም ጋር ተያይዞ ፕሮቲን በጣም ሲያንስ እሱን ለመተካትና ጉበት ላይ የሚከሰተው እብጠት እንዲጠፋ የሚሰጠው “አልቦሚን” የተሰኘው መድኃኒት መሆኑን ጠቅሰዋል።  

በሀገሪቱ በመድሃኒት አስመጪነት ፈቃድ የወሰዱትም ሆኑ ሌሎች በሀገሪቱ ያለውን የመድኃኒት ምርት ፍላጎት ያጤኑ ግለሰቦች ይህንን ክፍተት ለመሙላት “ወደ ጥቁር ገበያ ፊታቸውን በማዞር መድኃኒቶች በኮትንሮባንድ ገብተው በመሸጥ ላይ ይገኛሉ” ሲሉ የገለጹልን ደግሞ የግል ፋርማሲ ከፍተው በመዲናዋ የሚተዳደሩ የዘርፉ ባለሙያ ናቸው።

በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ የፋርማሲ መደብሮች ውስጥ ደረጃውን ያልጠበቀ እና በህገወጥ መንገድ የተመረተ አልያም የገባ መድኃኒቶች መኖራቸውን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ባለሞያ ለአዲስ ስታንዳርድ ጠቁመዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት በሀገሪቱ በህጋዊ መንገድ መድሃኒት ለማስገባት ፈቃድ የወሰዱ ድርጅቶችም እየተሳተፉበት ይገኛል ሲሉ የገለጹት ባለሙያው የውጨ ምንዛሬ እጥረቱ ይበልጥ በኮንትሮባንድ ለሚገቡ የመድኃኒት ምርቶች ሀገሪቱን ተጋላጭ አድርጓታል ሲሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገቡ መድሃኒቶችን እንዲቆጣጠር የተቋቋመው እና ስልጣን የተሰጠው፤ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፤ የተመረቱበት አገር ዕውቅና ያልሰጣቸው፣ አምራቻቸው የማይታወቅና በባለሥልጣኑ ያልተመዘገቡ መድኃኒቶች በብዛት በተለያየ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁሟል።

በኮንትሮባንድ ከሚገቡ መድኃኒቶች በተጨማሪ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገሪቱ መድኃኒት የማስመጣት ፈቃድ የተሰጣቸው አንዳንድ ድርጅቶች በሚያስገቡት በርካታ መድኃኒቶችም ፈዋሽ አይደሉም_ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር ሰለሞን ተዘራ ( ስማቸው የተቀየረ)

ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ አንደሚያሳየው 20 ከሚደርሱ የሀገር ዉስጥ የመድኃኒት አምራቾች ግብዓቶችን በመግዛት ያሰራጫል፤ አምራቾቹ ትልቅ የማምረት አቅም ቢኖራቸዉም ጥሬ እቃ የሚገዙበት የዉጭ ምንዛሬ አለመኖር ተግዳሮት እንደሆነባቸው አትቷል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለመንግስት የጤና ተቋማት የመድኃኒት ግዥ በየዓመቱ 15 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ ባሳለፍነው አመት ይፋ አድርጎ ነበር። በወቅቱ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ከውጪ ሀገራት 85 በመቶ የሚሆነውን መድኃኒት በማስገባት 15 ከመቶ የሚሆኑትን በራሷ አምርታ ታቀርባለች።

በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የመድኃኒት ፋብሪካዎች ከሚመረተው መድኃኒቶች በተጨማሪ ፍቃድ በተሰጣቸው አስመጪዎች አማካኝነት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ አንዳንድ መድኃኒቶች የፈዋሽነት ተግባር የሌላቸው መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ከማህበረሰቡም “መድሃኒቶቹ አይፈውሱም፣ አላሻለኝም” የሚሉ ቅሬታዎች በተለያዩ ግዜያት ይነሳል። 

የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ተዘራ (ስማቸው እንዲጠቀስ ባለመፈለጋቸው የተቀየረ) በላበራቶሪ በታገዘ ምርመራ ህመማቸው ታውቆ መድሃኒት የሚታዘዝላቸው ህሙማን የሚገዙት መድኃኒት ችግር ያለበት (ደረጃውን ባልጠበቀ ሁኔታ የተመረተ ወይንም ጭራሽኑ መድሃኒት ያልሆነ በህገወጥ መንገድ ተመርቶ የገባ) በመሆኑ ብቻ የህክምና ሰዎችን እጀሰባራ አድርጓል ሲሉ ይገልጻሉ።

የፈዋሽነት ችግሩ ከአመራረቱ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት የውሰጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ፤ በኮንትሮባንድ ከሚገባ በተጨማሪ በህጋዊ መንገድ በሀገሪቱ መድሃኒት የማስመጣት ፈቃድ የተሰጣቸው አንዳንድ ድርጅቶች በሚያመጡት መድኃኒቶች ላይም ችግሩ እንደሚታይ ጠቁመዋል።

እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት እና የልብ ህመም ታካሚዎች ለተከታታይ የሚወስዷቸው መድሃኒቶች ፈዋሽ ካልሆኑ ወዲያው ምልክቶች እንደሚታዩ ዶ/ር ሰለሞን ጠቁመዋል።

ዶ/ር ሰለሞን አክለውም፤ በቅርቡ በህክምና ባለሞያተኞች ችግር እንዳለባቸው የተለዩ እና ለሚመለከተው የሀገሪቱ ተቋም የምግብ እና መድኃኒት ተቆጣጣሪ ሪፖርት ተደርጓል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም እሳቸው በተሳተፉበት ሰሚናር ላይ የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር “ጋልቫኔዝ” የተባለ መድኃኒት ችግር አለበት ተብሎ ሪፖርት መደረጉን ገልጸዋል። 

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንን ጠይቀን፤ “ምንም አይነት ሪፖርት አልደረሰንም” ሲል አስተባብሏል።

በባለስልጣኑ የደቡብ ምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ገዛኽኝ እንዳለ፤ “ምንም አይነት መድኃኒት ከደረጃ በታች ነው ወይንም ችግር አለበት ተብሎ ለባለስልጣኑ የቀረበ ስሞታ የለም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

“እንደ የካንሰር በሽታ መድኃኒት አይነቶች፣ በኮንትሮባንድ የመግባት ሁኔታዎች ይታያሉ፤ ይህንን ለመግታት መግቢያ እና መውጫ ላይ በቂ የሆነ የቁጥጥር ስራ ይካሄዳል፣ ነገር ግን የሚገባበት መንገድ ይኖራል፣ ሲገኝ ግን ያንኑ እንዲወረስ እና እንዲወገድ የማድረግ ስራ ይሰራል” _ የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን

ማንኛው አይነት መድሃኒት ሀገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት እንደሚመዘገብ፣ ሳይንሳዊ ሂደቱን ተከትሎ ስለመመረቱ እንደሚጣራ፣ ግባአቶቹ ትክክለኛ ስለመሆናቸው እንደሚረጋገጥ እና ጥናት የተደረገበትን ሰነድ በመገምገም የገበያ ፈቃድ እንዲያገኝ ይደረጋል ሲሉ መድሃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ የሚተዋወቁበትን ሂደት አብራርተዋል።

ኃላፊው፤ መድሃኒት ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጣ ናሙና ተወስዶ የጥራት ምርመራ ይደረግበታል፤ ከተረጋገጠ በኋላ የገበያ ፈቃድ ይሰጠዋል፤ መግቢያ እና መውጫ ላይ ደግሞ አካላዊ ፍተሻ ይደረግበታል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ካጋጠመን የዶላር እጠረት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ካለው አንጻር ካየነው በተፈለገው ደረጃ መድኃኒቶች ሀገር ውስጥ አይገኙም፣ ሲሉ ገልጸው፤ የሚፈለጉ መድሃኒቶችን ሙሉ በሙሉ ለማግኘት ችግር እንዳለ መረጃው እንዳላቸውም ገልጸዋል። 

“እንደ የካንሰር በሽታ መድኃኒት አይነቶች፣ በኮንትሮባንድ የመግባት ሁኔታዎች ይታያሉ፤ ይህንን ለመግታት መግቢያ እና መውጫ ላይ በቂ የሆነ የቁጥጥር ስራ ይካሄዳል፣ ነገር ግን የሚገባበት መንገድ ይኖራል፣ ሲገኝ ግን ያንኑ እንዲወረስ እና እንዲወገድ የማድረግ ስራ ይሰራል” ሲሉ አብራርተዋል። 

ነገር ግን በሁሉም የውጭ አምራቾች ላይ እና አስመጪዎች ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ አቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል። 

“የህገወጥ መድኃኒት አቅርቦት የበዛ ነው የሚል የግምገማ ነጥብ የለኝም፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስናነጻጽረው በተሻለ ደረጃ ቁጥጥር ይደረጋል። ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነትን ለማረጋገጥ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚሰሩ በርካታ ስራዎች አሉ” ሲሉ ነግረውናል።

በአስመጪዎች በኩል የገባ ምንም አይነት ፈዋሽነቱ ጥርጣሬ ላይ የወደቀ መድሃኒት የለም ሲሉ የገለጹት አቶ ገዛኸኝ ነገር ግን ጅምላ አከፋፋዮች በተለያየ መንገድ የገቡ መድሃኒቶችን በጨረታ መልክ ለቸርቻሪዎች ሊያቀርቡ ይችላሉ፤ በዚህ መንገድ ለቸርቻሪዎች በኮንትሮባንድ የገቡ መድሃኒቶችን ያከፋፈሉ (ጅምላ አከፋፋዮች) ብለዋል። ያልተመዘገበ መድሃኒት ለጳውሎስ ሆስፒታል ጭምር ሲያከፋፍሉ የተገኙ አራት ጅምላ አከፋፋይ ድርጅቶች ፈቃዳቸው መሰረዙንም ጠቅሰዋል። 

የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱ በሚፈለገው መጠን አይደለም ሲሉ የገለጹት ኃላፊው፤ “ለአስመጪዎች በቁጥራቸው ብዛት ልክ እያዳረሰ አይደለም። በዚህም ምክንያት እጥረቶች ሊከሰቱ ይችላሉ” ብለዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button