አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በሰላም እጦት ችግር በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙት 996 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተከፈቱት 86ቱ ብቻ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ጌታሁን ፈንቴ፤ በዞኑ በዘንድሮ ትምህርት ዘመን 710 ሺህ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ መመዝገብ የቻሉት 70 ሺህ ብቻ ናቸው፤ 640 ሺህ ተማሪዎች ዛሬም የዕውቀት በራቸው ተዘግቶ ተበትነው ይገኛሉ” ብለዋል።
ተከፍተው ሥራ የጀመሩት ትምህርት ቤቶችም ከችግሮች የጸዱ አይደሉም ያሉት አቶ ጌታሁን ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡ ሕጻናት በየመንገዱ “መጽሐፍና ደብተራቸው እየተቀደደባቸው እና እየተደበደቡ አልቅሰው ይመለሳሉ” ሲሉ ገልጸዋል።
ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እንደላኩ የተሰማባቸው ወላጆችም እስከ “15 ሺህ ብር ቅጣት፣ ድብደባን ጨምሮ እስከ ግድያ የደረሰ ግፍም እንደተፈጸመባቸው” የትምህርት መምሪያ ኃላፊው አክለው ተናግረዋል።
የተበተኑ ልጆችን ሠብሥቦ የማስተማር ታሪካዊ ኀላፊነታቸውን የተወጡ መምህራንም የአካል እና የሕይወት መሥዋእትነት ከፍለዋል ብለዋል።
አቶ ጌታሁን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀው ቤት ሲውሉ በተለይም ሴት ልጆች “ያለዕድሜ ጋብቻ እየተፈጸመባቸው ነው” ሲሉ ገልጸው ወንዶቹም ቢኾኑ ዘመን በወለደው አጓጉል ቦታ እየዋሉ ለወላጆቻቸው የጭንቀት ምንጭ እየሆኑ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
“እንደ ክልል የገጠመው የሰላም እጦት ችግር ተምሮ የመለወጥ እና ተወዳዳሪ የመኾን ህልም ላይ ፈተና እየደቀነ ነው” ያሉት አቶ ጌታሁን በዞኑ በ2016 ዓ.ም ከ630 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከሚወዱት የትምህርት ገበታቸው ተነጣጥለው መክረማቸውን አስታውሰዋል።
የዞኑ የትምህርት ሥራ በዞኑ ማንም ሳያደናቅፈው እንዲቀጥል የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በየአካባቢው ከሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ሳይቀር ውይይት አድርገው እንደነበር አቶ ጌታሁን ለአሚኮ ተናግረዋል። የታጠቁ ኃይሎች ግን “የሚያዝዙን መሪዎቻችን ካልፈቀዱ በስተቀር ትምህርት እንዲከፈት አንፈቅድም” የሚል ምላሽ እንደሰጡም ገልጸዋል።
“ጥያቄዎች አሉ፤ ይኖራሉም። የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት ከተፈለገ ተወዳዳሪ፣ ተደማጭ እና ገዢ ሃሳብ ያለው ትውልድ መፍጠር ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ መማር እና መማር ግድ ይላል” ነው ያሉት አቶ ጌታሁን “ወቅታዊ ግጭት የነበረ፣ ያለ እና ሊኖርም የሚችል የሀገራት ታሪክ ቢኾንም መማር እና መለወጥን መጥላት ግን ከየትኛውም አካል የማይጠበቅ ድርጊት መኾኑን” አስምረውበታል።
በተመሳሳይ መልኩ በክልሉ ሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኙ 565 ትምህርት ቤቶች መካከል መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ የጀመሩት 192 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ በቅርቡ አስታውቋል።
በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት አለመጀመራቸው ይታወቃል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም. 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢያቅድም እስካሁን የተመዘገቡት ከ2 ሚሊዮን እንደማይበልጡ ገልጿል።አስ