ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት በ72 ሰዓታት ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ታዘዙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም፡- የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር በሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በ72 ሰዓታት ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበ፤ ዲፕሎማቱ አሊ መሃመድ አዳን ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ያዘዝኩት “ከዲፕሎማሲያዊ ሚናቸው ጋር የማይጣጣሙ ተግባራት እየፈጸሙ” በመሆኑ ነው ሲል አስታውቋል።

በሞቃዲሾ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአማካሪነት በመስራት ላይ የነበሩት አሊ ሞሃመድ “በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የተደረሰውን የቪየና ስምምነትን የሚጥስ” ተግባር ፈጽመዋል ሲል ሚኒስቴሩ ትላንት ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው አትቷል።

በቪየና ስምምነት መሰረት በሌላ ሀገር የሚመደብ ዲፕሎማት መቀመጫ ያደረገውን ሀገር ህግ እንዲያከብር እና በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ያዛል።

ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት ሀገሬን ለቀው እንዲወጡ የ72 ሰዓታት ግዜ ሰጥቻለሁ ያለው መግለጫው

እርምጃው የሶማሊያን ብሔራዊ ሉዓላዊነቷን ባስጠበቀ እና “አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መመዘኛዎችን በማክበር የተደረሰ ነው ሲል አትቷል።

ውሳኔው ሶማሊያ ሉዓላዊነታን በጠበቀ መልኩ አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮልን ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲል አስታውቋል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው ዲፕሎማቱ ስለፈጸሙት የህግ ጥሰት ምንም ያለው ነገር የለም።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ባለፈው አመት 2016 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በሞቃዲሾ የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሞሃመድ ዋሬ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ የ72 ሰዓት ግዜ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሩን ለምክክር በሚል መጥራቱን ተጠቁሟል።

“እርምጃው የተወሰደው የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክን ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነጻነት እና ግዛታዊ አንድነት ለማስጠበቅ ነው” ሲል ይፋዊ መግለጫው አትቷል።

ውሳኔው የተላለፈው የሀገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ መንግስትን “የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የውስጥ ጉዳይ የተጻረረ” “ተግባር” ተከትሎ ነው በማለት የገለጸ ሲሆን በዝርዝር የጠቀሰው ነገር ግን የለም።

ከሀገራቸው መንግስት ጋር እንዲመክሩ በሚል ሞቃዲሾን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል ያለው ዘገባው በተጨማሪም የሶማሊያ መንግስት በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ እና በፑንትላንድ የሚገኙትን ቆንስላ ጽ/ቤቶችን እንዲዘጉ ማድረጓንም ጠቁሟል።

ሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን ሙክታር ሞሃመድ ዋሬ ከሞቃዲሾ ያባረረችው መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑንም በዘገባው ተጠቅሷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button