ማህበራዊ ጉዳይዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች “የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ዜጎችን አስገድዶ በመሰወር፣ ያሉበት ሳይገለጽ ለተራዘመ ግዜ ለእስር ዳርገዋል” - ኢሰመኮ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ፣ ኦሮምያ እና አማራ ክልል አሁንም “በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ተይዘው ያሉበት ሳይገለጽ ለተራዘመ እስር የተዳረጉ ሰዎች መኖራቸውን” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “አሁንም ያሉበት ሁኔታ የማይታወቁ ሰዎችን ጉዳይ በተመለከተ የጸጥታ አካላቱ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ” ጥሪ አቅርበዋል።

ኢሰመኮ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ መሆናቸው የተገለጸ ከ52 በላይ የሆኑ ሰዎችን የተመለከቱ አቤቱታዎችን መመርመሩን ጠቁሞ ከ1 ወር እስከ 9 ወር በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ከቆዩ በኋላ መለቀቃቸውን አስታውቋል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ፤ ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ በተራዘመ እስር፣ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች፣ ብሎም በአስገድዶ መሰወር ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን ጠቁሟል።

ኮሚሽኑ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዐይን ምስክሮችን እና የተለቀቁ ሰዎችን በማነጋገር አሰባሰብኩት ባለው መረጃ እንዳስታወቀው፤ ተጎጂዎች በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎችና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት ተገቢውን የሕግ ሥነ ሥርዓት ባልተከተለ ሁኔታ በግዳጅ የተያዙ መሆናቸውን አመላክቷል።

ተጎጂዎች በእስር የቆዩበትን ቦታ የማያውቁ፣ በቂ ምግብና ውሃ የማይቀርብላቸው የነበሩ፣ እንዲሁም ለየብቻቸው ተለይተው ተይዘው የቆዩ መሆናቸው ተነስቷል።

በተጨማሪ ተጎጂዎቹ ሲለቀቁ “በምሽት ዐይናቸው ተሸፍኖ በተሽከርካሪ ከተጫኑ በኋላ በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች እንዲወርዱ ተደርገው እና ለመጓጓዣ በሚል ከ300 እስከ 1000 ብር ተሰጥቷቸው” እንደነበረ ተጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢሰመኮ በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ወይም ያሉበት ሳይታወቅ በተራዘመ እስር ሁኔታ ቆይተው የተለቀቁ ሰዎችን ታሪክ በሪፖርቱ አካቷል።

ለአብነትም አቶ መቼምጌታ አንዱዓለም የተባሉ  ባለትዳርና የ2 ልጆች አባት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነሐሴ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ “ብስራተ ገብርኤል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የታክሲ አገልግሎት ከሚሰጡበት አካባቢ ከነተሽከርካሪያቸው የሲቪል ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት ተወስደው፣ በተለምዶ “ራሺያ ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኖሪያ ለ7 ወራት ከቆዩ በኋላ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም መለቀቃቸውን ገልጸዋል።

አቶ መቼምጌታ ተይዘው የቆዩበትን ሁኔታ በተመለከተ “በቂ ምግብ የማይቀርብበት፣ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር ያለበት፣ ሰዎች ሕመም ሲገጥማቸው ሕክምና ማግኘት የማይችሉበት፣ ምንም ዐይነት የቤተሰብ ጥየቃ የማይፈቀድበት እንዲሁም ከፍራሽ ውጪ የመኝታ አልባሳት የሌሉበት” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም ለ7 ወራት ያህል በእስር ላይ በቆዩበት ወቅት በቦታው በአጠቃላይ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች ተይዘው መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

ኢሰመኮ “ከቀናት እስከ ወራት ለቆየ፣ ትክክለኛ አድራሻውን ማወቅ ባልተቻለ እና መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች በእስር ቆይተው ከተለቀቁ ሰዎች መካከል፣ የያዟቸው ሰዎች ገንዘብ ከፍለው ሊለቀቁ የሚችሉ መሆናቸውን የገለጹ እና አንዳንዶቹም በቤተሰብ አማካኝነት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠር ብር የከፈሉ መሆኑን ያስረዱ መኖራቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት እና አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን በተጨማሪ የሚያጠናክር ነው።” ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button