ዜናፖለቲካ

ዜና: ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ወታደር አዋጭ የሆኑ ሃገራት በሶማሊያ በአዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ለመቀጠል ያላቸውን 'ፈቃደኝነት እና ዝግጁነት' ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9/ 2017 ዓ.ም:- ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ወታደር አዋጭ የሆኑ ሀገራት የመከላከያ ሚንስትሮች በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ጥረታቸውን በአዲሱ ተልዕኮ ለመቀጠል ያላቸውን “ፍላጎት እና ዝግጁነት” ገልጸዋል።

ሚንስትሮቹ ይህን የገለጹት ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ ጋባዥነት ከተዘጋጀው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ ጎን ለጎን የተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው።

ስብሰባው ከብሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ የተውጣጡ የመከላከያ ሚንስትሮችን አካቷል ተብሏል።

አዲስ ስታንዳርድ የተመለከተው የጋራ መግለጫ እንዳስታወቀው ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ወታደር አዋጭ የሆኑ ሃገራት በሶማሊያ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና ሀገሪቱን በማረጋጋት የከፈሉትን መስዋዕትነት እውቅና ሰጥቶ፤ ለሶማሊያ ፌደራል መንግስት ተቋማትን በማጎልበት እንዲሁም በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ አድረጓል ብሏል።

ሚኒስትሮቹ በመግለጫቸው በፋይናንስ ዘላቂነት ላይ ያላቸውን ስጋት አንስተው፣ “ለአትሚስ እና አውሶም ተገማች፣ በቂ እና ተለዋዋጭ የገንዘብ ድጋፍ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።” ብለዋል።

አክለውም አሁን ላይ ያለውን የበጀት እጥረት መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

የመከላከያ ሚንስትሮቹ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ወይም በምህጻሩ አውሶም (AUSSOM) መመስረትን በተመለከተ “ከአትሚስ የተወሰዱ ልምዶች በቀሪው ሂደት ውስጥ በጥልቀት የታሰቡ ናቸው።” በማለት አጽንኦት ሰጥተው፣ በአውሶም ምስረታ ወቅት ወታደር አዋጭ የሆኑ ሃገራትን ማማከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሚኒስትሮቹ ስብሰባ የተካሄደው በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት እየተባባሰ በመጣበት እና ከአትሚስ ሽግግር ጋር የተያያዙ ፈተናዎች በበዙበት ወቅት ነው።

ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ አትሚስን ለመተካት በተዘጋጀው የአፍሪካ ህብረት በሚመራው ሃይል ተሳታፊ እንደማትሆን አስታውቃለች።

ግብፅ ወደ ሞቃዲሾ ወታደሮችን እና የጦር መሳሪያ ጭነቶችን መላኳ ሁኔታውን ​​አባብሶታል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በአትሚስ ሽግግር ስጋት እንዳላት በመግለጽ ሁኔታውን ለቀጣናው “በአደጋ የተሞላ” ስትል ገልጻዋለች።
በቅርቡ ግብፅ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ በአስመራ የሶስትዮሽ ስብሰባ አድርገው የሶማሊያን የየብስ እና የባህር ድንበሯን የመጠበቅ አቅም ለማሳደግ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ መስማማታቸው ይታወሳል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button