ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18/ 2017 ዓ/ም፦ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞን ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኘው የባቄሎ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው ያሉ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ከዚህ ቀደም በግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ሲሰጥ የነበረው እርዳታ መቆሙን ተከትሎ የምግብ አቅርቦት እጥረት መኖሩን አቶ አክሊሉ የተባሉ ተፈናቃይ ገልጸዋል።

“ካምፓችን ውስጥ የምግብ እጥረት አለ። ከዚህ በፊት በግል ምግብ ሲረዱ የነበሩ ድርጅቶች አሁን ላይ የሉም። አሁን ከመንግሥት በኩል በየ45 ቀኑ የሚሰጠን እርዳታ ብቻ ነው ያለው። ለወላዶች እና ለአቅመ ደካሞች ከዚህ በፊት በግብረ-ሠናይ ተቋማት የሚሰጠው ድጋፍ በምን ምክንያት እንደሆነ ባላውቅም ቆሟል” ብለዋል።

አቶ አክሊሉ አክለውም ባቄላ በተሰኘው መጠለያ ጣቢያ ውስጥ 5100 ተፈናቃዮች እንደሚገኙና ለሁሉም ተረጂ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ህክምናን በተመለከተ “ጎል” የተሰኘ ግብረ-ሠናይ ድርጅት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከእሱ ውጪ የደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሮ ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

ሌላኛው አስተያየታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጹ አቶ መለሰ ጌታሁን የተባሉ ተፈናቃይ በበኩላቸው እንደገለጹት በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ 5330 የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከነዚህም ውስጥ 4260 የሚሆኑት በየወሩ ከመንግሥት የሚቀርበውን እርዳታ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ይሁንና 714 የሚደርሱ አባዎራወች አሁን ላይ እርዳታ እንደተቋረጠባቸው ተናግረዋል።

“አሁን ላይ በመጠለያ ጣቢያው እርዳታ የማይሰጣቸው 714 አባወራዎች ይገኛሉ። ከዚህ በፊት ተፈናቃዮቹን የመመለስ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። በዚያ ወቅት የተመለሱ ነበሩ። ነገር ግን ከእነዚህ ተፈናቃይ ውጪ ያሉት አሁንም የጸጥታ ስጋት አለብን ብለው እዚሁ የተቀመጡት ናቸው እርዳታ የማያገኙት።” ያሉት አቶ መለሰ አክለውም ተፈናቃዮቹ ከኦሮሚያ ክልል በኩል የኛ ተፈናቃይ አይደሉም በሚል ስማቸው እንዲወጣ በመደረጉ ምክንያት ለዚህ ችግር መዳረጋቸውን አስረድተዋል።

“ከዚህ ቀደም እርዳታ ሲሰጡ የነበሩ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች አሁን ድጋፋቸውን በማቆማቸው እዚሁ ባለን ነገር እየተጋገዝን ነው እየኖርን ያለነው” ብለዋል።

ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን በሚገኝ መጠለያ ተጠልለው ከነበሩ እና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከተደረጉ አባወራ መካከል የሆኑት አቶ የሱፍ ሙሐመድ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት፤ ከመጠለያ ጣቢያው ከለቀቁ በኋላ ወደ ቀያቸው ሲመለሱ የተነገራቸውና ቦታው ላይ ሲደርሱ የተመለከቱት ለየቅል መሆኑን ያብራራሉ።

“የካቲት ወር 2016 ዓ.ም ነው፤ ከመጠለያው የወጣነው። መስራት ትችላላችሁ ተመለሱ እስከ መቼ ትለምናላችሁ ብለውን ነበር የተመለስነው። ከእኔ ጋራ አብረው ከዛ የመጣነው 33 እንሆናለን። በሶስት ዙር ነው ተጭነን የመጣነው።” ያሉት አቶ የሱፍ አክለውም ከተመለሱም በኋላ በወረዳው እርዳታ ኑሯቸውን እየገፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“ያለንበት የሌቃ ዱለቻ ወረዳ በወር 15 ኪሎ ዱቄት እየሰጠን በዛ እርዳታ ነው ያለነው አሁንም። መጠለያ ተሰርቷል ብለው በሚዲያ አስተላልፈው ካበቁ በኋላ መጥተን ስናየው መጠለያ የተባለው ነገር እንደ ለቅሶ ቤት ሸራ ነገር ወጠር አድርገው የሰሩትን ነው። እዛ ካስቀመጡን በኋላ ቡና ቁርስ ብለው ሰብስበውን ሁሉም የዘመድ ቤት አፈላልጎ እንዲጠጋ ነገሩን። እኛ ደግሞ ዘመድም የለንም።” ያሉት አቶ የሱፍ አያይዘውም “ከገባን ጀምሮ እስከ አሁን ቤት ኪራይ እየከፈልን ነው ያለነው። ሥራ ምንም ነገር የለም። ያው ካለችን በወር ከምትሰጠን ዱቄት ነው እየቀነስን የምንከፍለው።” ብለዋል።

“የምግብ እጥረት አለ። የሚሰጠን ምግብ ሽሮ በርበሬ ሽንኩርት ያካተተ ተመጣጣኝ አይደለም። በጣም እየተጎዳን ነው ያለነው። በወር ከምትሰጠን ከዛች ዱቄት ለቤት ኪራይ ስንከፍል፤ ለበርበሬ ስንከፍል ማስፈጫ ስንል በጣም ተቸግረን ነው ያለነው” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

አክለውም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሁኔታውን ተገንዝበው እርዳታ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀው፤ “መንግሥት ዞር ብሎ ይመልከተን” ሲሉ ተማጽነዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button