ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ በአማራ ክልል ባሳለፍነው እሁድ በተካሄዱ ውጊያዎች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19/2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በሶስት ዞኖች እሁድ ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄዱ ውጊያዎች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ውግያው በደቡብ ወሎ፣ ምሥራቅ ጎጃም እና አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን መካሄዱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ነዋሪ፤ ባሳለፍነው እሁድ በደበቡ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ሮቢት በሚባል ስፍራ ለሰዓታት የዘለቀ ከባድ የተኩስ ልውውጥ እንደነበረ ገልጸዋል።

“ንጋት ላይ ነው ተኩሱ የተጀመረው። ከዚህ በፊት ግጭቶች በተለያዩ ጊዜያት ነበሩ። የእሁዱ ዕለት ግን ለየት ያለና ከባድ ነበረ። መሳሪያ ሲተኮስ ነው የዋለው” ያሉት ነዋሪው አክለውም ከግጭቱ በኋላ በርካታ ተዋጊዎች “ሙትና ቁስለኛ ሆነው በመኪና ሲመላልሱ” መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ነዋሪው ተኩሱ ጋብ ካለ በኋላ “የጸጥታ ሃይሎች በርካታ ወጣቶችን ከየሰፈሩ እየወሰዱ እንደነበረ” ገልጸው አሁንም በአከባቢው ያለው “አፈሳ” መቀጠሉን ጠቁመዋል።

ሌላኛው ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ስር በምትገኘው አዲስ ቅዳም ከተማ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው ባሳለፍነው እሁድ ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ መዋሉን ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል። 

“እሁድ ሙሉ ቀኑን ውጊያ ሲካሄድ ነው የዋለው። በክላሽ እና በድሽቃ ነው የነበረው። ቤተክርስትያን የነበረው እዛው፤ ሌላውም ባለበት በር ዘግቶ ነው የዋለው” ያሉት ነዋሪው አያይዘውም በእሁዱ ዕለት ውጊያ እሳቸው ካሉበት አከባቢ ብቻ 6 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ነዋሪው አክለውም በአከባቢው አሁን ላይ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸው ግጭቶች ያገረሻሉ በሚል ስጋት በርካታ ሰዎች ወደ አጎራባች ገጠራማ አከባቢዎች እየሸሹ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ቀራንዮ ከተማ እሁድ ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም መካሄድ የጀመረው ውጊያ እስከ ትናንትና ማለትም እስከ ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ መቀጠሉን የስፍራው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

“ሞጣ ላይ በከባድ መሣሪያ ተኩስ ነበር ነበር። የት እንደሚያርፍ አናውቅም። እኛ ካለንበት ራቅ ብሎ ማዶ ነው የሚወነጨፈው። ግማሹ የሰዎች ቤት ላይ ነው የወደቀው ይላል። ብቻ ነገሩ።” ያሉት ነዋሪው አክለውም በቀጠለው ውጊያ የተነሳ ትራንስፖርትን ጨምሮ ሌሎች እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ተናግረዋል።

አያይዘውም በአሁኑ ሰዓት የከባድ መሣሪያ ድምጽ ባይሰማም አልፎ አልፎ የተኩስ እሩምታዎች እንዳሉ ገልጸው በእሁዱ እና ሰኞ ዕለቱ ግጭት የተነሳ በአከባቢው ያለው ውጥረት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ነዋሪው አክለውም በውጊያው መሃል በተባራሪ ጥይት ተመተው ህይወታቸውን ያጡ እና ቀብራቸው ገና ያልተፈጸሙ ሰላማዊ ሰዎች መኖራቸውን እንደሰሙ ገልጸዋል። ይሁንና ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ያልገለጹት እኒሁ ነዋሪ ሁኔታውን “አስከፊ የእልቂት ጊዜ” ሲሉ ገልጸውታል።

በተጨማሪ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ በተደጋጋሚ እያገረሹ በሚካሄዱት ግጭቶች የተነሳ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ተባብሶ በቀጠለው ግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውም ተነግሯል።

ለአብነትም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙት 996 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተከፈቱት 86ቱ ብቻ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ጌታሁን ፈንቴ፤ “በዞኑ በዘንድሮ ትምህርት ዘመን 710 ሺህ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ መመዝገብ የቻሉት 70 ሺህ ብቻ ናቸው፤ 640 ሺህ ተማሪዎች ዛሬም የዕውቀት በራቸው ተዘግቶ ተበትነው ይገኛሉ” ብለዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በበኩሉ በ2017 ዓ.ም. 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢያቅድም እስካሁን የተመዘገቡት ከ2 ሚሊዮን እንደማይበልጡ መግለጹ ይታወሳል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button