አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 16 2015 ዓ.ም፡- በሲዳማ ክልል ከብልሹ አሰራርና ከስርቆት ጋር በተያያዘ 10 ከፍተኛ አመራሮች ከሃላፊነት እንዲነሱ መደረጉንና ተጨማሪ 25 ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የክልል መንግስት አስታወቀ፡፡
የሲዳማ ክልል የ2015 ዓ.ም የፓርቲና የመንግስት ስራዎች አፈፃፀም የግምገማና የ2016 ዓ.ም የዕቅድ ፈፃሚ ማዘጋጃ መድረክ የማጠቃለያ መርሃ ግብር በትላንትናው እለት ተካሄዷል፡፡
በመድረኩ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባለፉት ወራት ውስጥ እንደ ወረርሺኝ ግብዓትን ለህዝብ ሳይደርስ በህገወጥ መልክ የመሸጥ አዝማሚያ ታይተዋል ሲሉ ገልፀው 97 ሰዎች ላይ በተለይ ከማዳበሪያ ግብዓት ጋር ተያይዘው ማስረጃዎች በማሰናዳት ለህግ እንዲቀርቡ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ሁለት የወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ በየደረጃው ተባባሪ የሆኑ ግለሰቦችን በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓልም ነው ያሉት።
ሀዋሳ ከተማ ላይም ከፍተኛ ሌብነትና ብልሹ አሰራር መታየቱን በመግለፅ የግምገማው መድረክ እየተካሄደ ባለበት ከተጠያቂነት ለማምለጥ አቋርጠው በመውጣት የሸሹ ግለሰቦች መኖራቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።
የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በመድረኩ እንደገለፁት የዚህ ግምገማ ዋና አላማው ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን አጥብቀው የሚቃወሙ አመራሮችን ለመፍጠር እና የያዝነውን የልማት ጎዳና አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል ለማድረግ ነው ብለዋል።
በስራችን ላይ የታዩ ጉድለቶችን በመለየት ይህ ተግባር እንዳይቀጥል የተደረገ እና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ በሌብነትና በብልሹ አሰራር ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
መድረኩ ለተከታታይ አስር ቀናት የተካሄደ ሲሆን አመራሩ በሰፊ እራሱን ያየበት እንደሆነ ተገልጿል።አስ