ዜናፖለቲካ

ዜና: "የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ መስፈሩ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣም፣ እንዲያውም የአልሸባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር አድርጓል" - ሶማሊያ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም፡- ባለፉት ግዜያት የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ መስፈሩ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣም እንዲያውም የአልሸባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር አድርጓል ሲል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሶማሊያ በቀጣይ ከአፍሪካ ሀገራት ተወጣጥቶ ተልዕኮ ተሰጥቶት በግዛቴ በሚሰፍረው ጦር ዙሪያ የትኞቹ ሀገራትን ማዋጣት አለባቸው የሚለውን የምመረጠው እራሴ ነኝ ስትል ገለጸች።

ሶማሊያ ይህንን የገለጸችው የአፍሪካ ህብረት በሚያሰማራው ጦር ዙሪያ ኢትዮጵያ ስለሚኖራት ሚና እና ስለሶማሊያ ሉዓላዊነት በሚያትተው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ ነው።

የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ እና የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጥ ይሻል ያለው መግለጫው በዚህም ሳቢያ በቀጣይ ከአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ተሰጥቶት በሶማሊያ የሚሰፍረው ጦር የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ላይ በማተኮር ተልዕኮውን እንዲወጣ ይደረጋል ሲል ገልጿል።

ከሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ወደ በሶማሊያ አፍሪካ ህብረት ማረጋጊያ ተልዕኮ (AUSSOM) በሚሸጋገርበት ወቅት “የተልእኮው አቅጣጫ በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ አተኩሮ በግልጽ እንዲመራ ይደረጋ” ሲል አትቷል።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በተናጠል የምትወስዳቸው እርምጃዎች የሀገራችንን ሉዓላዊነት የጣሰ ነው፣ ይህም በሀገሪቱ ላይ ያለንን እምነት የሸረሸረ ነው ሲል የገለጸው መግለጫው ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት በአብነት አስቀምጧል፤ በሰላም ማስከበር ሂደት ላይ ወሳኝ እና አስፈላጊ የሆነውን መተማመን እንዳይፈጠር አድርጓል ሲል ኮንናል።

ይህም በቀጣይ ከአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ተሰጥቶት በሶማሊያ በሚሰፍረው ጦር ውስጥ የሚሳተፉ ሀገራትን በጥንቃቄ እንድንመርጥ አድርጎናል ሲል አስታውቋል። በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ማረጋጊያ ተልዕኮ (AUSSOM) ላይ የሚሳተፉ አጋር ሀገራት በሶማሊያ ደህንነት እና ልማት ግብ ጋር የሚጣጣሙ እንዲሆኑ ለማረጋገጥ ይበልጥ ስለታዊ የሆነ ምርጫ ጦር በሚያዋጡ ሀገራት ዙሪያ ይደረጋል ሲል ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ወደ ቀጣዩ የህብረቱ ተልዕኮ ምዕራፍ እያመራን ባለበት ወቅት ሶማሊያ ሉዓላዊ ሀገር እንደመሆኗ የትኛው ሀገር መሳተፍ እንዳለበት የመወሰን ስልጣን እንዳላት ደጋግሞ መናገር አስፈላጊ ነው ስትልም አስታውቃለች።

በተልዕኮው ሰራዊት የሚያዋጡ ሀገራት ዙሪያ የሚሰጠው ውሳኔ ከሶማሊያ ብሄራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነቷን ከማስጠበቅ ጋር መጣጣም አለበት ሲልም መግለጫው አሳስቧል።

በተልዕኮው ሰራዊት በሚያዋጡ ሀገራትን ምርጫ በተመለከተ ሶማሊያ የመሪውን ሚና እየተጫወተች ከአፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር  ለመስራት ቁርጠኛ ናት ሲል መግለጫው አካቷል።

የሶማሊያን መጻኢ እድል እና ደህንነት ላይ ተጽዕኖ የሚኖረው ምንም አይነት ውሳኔ ለመቀበል ድርድር አታደርግም ሲል አትቷል። ሶማሊያ ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች እንድትሆን ሁሉም አጋሮቻችን እነዚህን መርሆዎች እንዲያከብሩ እንጠይቃለን ብሏል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ወታደር አዋጭ የሆኑ ሀገራት የመከላከያ ሚንስትሮች በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ጥረታቸውን በአዲሱ ተልዕኮ ለመቀጠል ያላቸውን “ፍላጎት እና ዝግጁነት” መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ሚንስትሮቹ ይህን የገለጹት ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ ጋባዥነት ከተዘጋጀው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ ጎን ለጎን የተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ ባወጡት የጋራ መግለጫ ነበር።

ስብሰባው የብሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ የተውጣጡ የመከላከያ ሚንስትሮችን ተሳትፈዋል።

አዲስ ስታንዳርድ የተመለከተው የጋራ መግለጫ እንዳስታወቀው ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ወታደር አዋጭ የሆኑ ሃገራት በሶማሊያ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና ሀገሪቱን በማረጋጋት የከፈሉትን መስዋዕትነት እውቅና ሰጥቶ፤ ለሶማሊያ ፌደራል መንግስት ተቋማትን በማጎልበት እንዲሁም በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ አድረጓል ብሏል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሸክ ሀሰን ከባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ቀናት ጀምሮ በሀገራቸው ሰላም ማስከበር ሂደት ወታደሮቻቸውን ባሰማሩ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጉብኝት እያካሄዱ እንደሚገኙ መዘገባችንም ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ በኡጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ጂቡቲ ቅዳሜ እና እሁድ ጉብኝት ያካሄዱ ሲሆን ትላንት ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም በኬንያ ጉብኝት ማካሄዳቸውም ታውቋል።  

የሶማሊያ ፕሬዘዳንት ጉብኝት ኢትዮጵያን አያካትትም ሲሉ ቃል አቀባያቸው አብዱልቃድር ዲጌ መግለጻቸውን ቪኦኤን ዋቢ በማድረግ በዘገባችን ተካቷል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button