ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በሰሜን ጎጃም ዞን ህጻናትን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰላማዊ ሰዎች "በመንግስት የጸጥታ አካላት" መገደላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25/ 2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በሰሜን ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ ብራቃት ከተማና በአካባቢው በሚገኙ ስንኳ፣ አርሴማና ፍጣ በተሰኙ ስፍራዎች ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም “የመንግስት የጸጥታ አካላት ቤት ለቤት እና መንገድ ላይ” ፈጸሙት በተባለ ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ አንድ ነዋሪ፤ በዕለቱ ከጠዋት አንስቶ ለረዥም ሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ “በመከላከያ ሰራዊቱ እና በአድማ ብተና ሀይሎች መካከል” በብራቃት ከተማ ሲደረግ እንደነበር ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

የተኩስ እሩምታው ካቆመ በኋላ “የመንግሥት የጸጥታ አካላት በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች በመንቀሳቀስ ያገኙትን ሰው ወደ መረሸን ገቡ” ብለዋል።

“ግድያውን የጀመሩት ከብራቃት ከተማ በምስራቅ በኩል ሲሆን ከከተማው ውጭ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ አጣሪ የተባለች ተራራ እስኪደርሱ እየገደሉ ነው ያለፉት” ሲሉ ገልጸዋል። 

በመጀመሪያ ውጊያው የተቀሰቀሰው ከከተማዋ በስተምስራቅ 2 ኪ.ሜ ላይ በሚገኘው ፍጣ ሚካዔል ቤተ ክርስቲያን እንደነበረ የገለጹት ነዋሪው አክለውም ቄስ ዋሴ ይግዛው የተባሉ የቤተ-ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪን ጨምሮ 46 ሰላማዊ ሰዎች በ”መንግሥት የጸጥታ አካላት” መገደላቸውን ጠቁመዋል።

ከተገደሉት ሰዎች መካከልም መንገድ ላይ ከወፍጮ ቤት ሲመለሱ የነበሩ እናቶች፣ ቤት ዘግተው የተቀመጡ ሰዎች፣ የአዕምሮ ህሙማን እና ህጻናት ሳይቀር እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

ነዋሪው አያይዘውም “ከሟቾች መካከል አቶ ገረም ይመኑ የተባሉ የደም ግፊት መድኃኒት የሚወስዱ እና የህክምና ክትትል የነበራቸው አዛውንት አቶ ቻይና ይመኑ የተባሉ ወንድማቸው በተተኮሰባቸው ጥይት ተመትተው ሲወድቁ ሰምተው ከቤታቸው ሲወጡ እርሳቸውንም ገደሏቸው” ሲሉ አብራርተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አክለውም “ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ሰው እየጮኸ ይሰማን ነበር ከዛ የግቢያችን ሰወች ይወጣሉ። ከዛ ሰው እንዳናይ ብለዋል እና አትውጡ ተባለ ብለው መጡ።” ያሉት ነዋሪው የመንግስት የጸጥታ አካላት የሟቾች አስከሬን አይነሳም ብለው መከልከላቸውን ተከትሎ አስከሬኖቹ አድረው በማግስቱ ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም መነሳታቸውን ተናግረዋል።

አስከሬኖቹ የተነሱትም በማግስቱ የመከላከያ ሠራዊት ከተማዋን በመልቀቅ ከከተማዋ 4ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው የምድረ ገነት ቀበሌ አጣሪ የተባለ ተራራ ላይ መስፈሩን ተከትሎ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአብዛኞቹ ሟቾች የቀብር ስነ-ስርዓትም ከተማው ውስጥ ባለ የመድኃኒዓለም ቤተክርቲያን በጅምላ የተፈጸመ ሲሆን የቀሪዎቹ ደግሞ በየቤተ ክርስቲያናቸው ስንኳ ጊዎርጊስ፣ ቦረቦር ስላሴ እና አንድ ለስራ ከተማው መጥቶ የተገደለ ግለሰብ ደግሞ በፍጣ ሚካዔል መፈጸሙን ነዋሪው አክለው ገልጸዋል።

እኚሁ ነዋሪ የጅምላ ግድያው በተፈጸመበት ዕለት “የፋኖ ታጣቂዎች በአከባቢው እንዳልነበሩ” ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በትናንትናው ዕለትም በከተማዋ ዙርያ በሚገኝ ገብርዔል በተባለ ቦታ ከ8-12 ሰዓት የቆየ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ገልጸው ቦታው ምናልባትም ባለፈው አመት 11 የቤተ-ክነት ተማሪዎችና አንድ የደብሩ አገልጋይ የተገደለበት ቦታ ሳይሆን እንደማይቀር ተናግረዋል። 

“ድባቡ በጣም ይከብዳል። ጭንቀት ላይ ነን።” ሲሉ ስለ ሁኔታው አስረድተዋል።

ሌላኛው ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ ነዋሪ በበኩላቸው፤ ከመራዊ ከተማ 21 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የብራቃት ከተማ ዙርያ መጋቢት 22 ቀን ከጠዋት አንስቶ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ “የአድማ ብተና ሀይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በመቀናጀት ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር” ግጭት ውስጥ መግባታቸውን አስረድተዋል።

ተኩሱ 7 ሰዓት ገደማ ከበረደ በኋላም የ” መንግሥት የጸጥታ አካላት ወደ ከተማዋ ዘልቀው በመግባት ያገኙትን ሰው ወደ መግደል ገቡ” ብለዋል።

በዚህም 40 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ከነዚህም ውስጥ አጎራባች ከሆኑ ስፍራዎች ለወፍጮ እና ለሌላም ጉዳይ ወደ ከተማዋ የገቡ እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ እናቶች፣ ህጻናት፣ ሴቶች፣ የቤተክርስትያን አስተዳደሪ እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

በተጨማሪም “የተዘጋ ቤት እየተከፈተ ግድያው ይፈጸም ነበረ” ሲሉ ስለሁኔታው አስረድተዋል።

የሟቾች የቀብር ስነ-ስርዓትም ነዋሪው በከፍተኛ ስጋት እና ጭንቀት ባንዣበበበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በሚካኤል እና በመድሀኒዓለም አብያተ ክርስቲያናት በጅምላ ከ8-12 እየተደረገ መቀበራቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም አሁን ላይ ግጭቶች አሁን ከአሁን እንደአዲስ ያገረሻሉ በሚል ስጋት የከተማዋ ነዋሪ አጎራባች ወደ ሆኑ የገጠር ቀበሌዎች በመሸሽ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ወታደራዊ ግጭት ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ለህልፈት እየተዳረጉ ይገኛል።

ለአብነትም በቅርቡ በክልሉ ምስራቅ ጎጃም ዞን ነፍሴ ሳር ምድር ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ ግጭት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል

እንዲሁም ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ሸባ በተሰኘች ቀበሌ በእርሻ አውድማ ላይ የነበሩ 11 ሰዎች  “በመንግሥት የጸጥታ አካላት” መገደላቸውን  አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል

በተጨማሪም በምዕራብ ጎጃም ዞን  ጃቢ ጠህናን ወረዳ ጅማት እንቆቅማ ቀበሌ አርብ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ “በከባድ መሳሪያ” በታገዘ ውጊያ የ14 ዓመት ታዳጊ እና መነኩሴን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል

በወቅቱ ሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በአርሶ አደሮች ሰብል ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት መድረሱን ዘገባው አመልክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button