ዜናጤና

ዜና፡ በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 83 ሰዎች በወባ በሽታ ህይወታቸው ማለፉን ኢኒስቲትዩቱ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6/2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 83 ሰዎች በወባ በሽታ ምክኛት ህይወታቸው ማለፉን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቀ። ይህም ካለፈው አመት ተወሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር የሞት መጠኑ በ68 በመቶ ጨምሯል ብሏል። 

82 በመቶ የአማራ ክልል ህዝብ ለወባ በሽታ የተጋለጠ መሆኑን ያስታወቀው ኢኒስቲትዩቱ በክልሉ 1ሚሊዮን አራት መቶ ሀምሳ ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን አስታውቋል። ይህም ካለፈው አመት ተወሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር በ559.8 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጿል።

99.4 በመቶ ወረዳዎች የወባ ስርጭት ያለባቸው ሲሆኑ 40 ቀዳሚ ወረዳዎች የክልሉን 69 በመቶ የወባ ስርጭት እንደሚሸፍኑም የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት ባጋራው መረጃ አመላክቷል። 

በተጭማሪም 82.5 በመቶ ቀበሌዎች ወባማ ናቸው፣ 80 በመቶ የሚሆነው የቆዳ ስፋት በሽታው መተላለፊያ ምቹ ነው ያለው መረጃው 90 በመቶ የወባ ስርጭት የምዕራቡ አማራ ይሸፍናል ሲልም ገልጿል።

በቅርቡ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አሥተባባሪ እና የክልላዊ የወባ መከላከል ግብረ ኀይል ሠብሣቢ የሆኑት ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር ) የቁጥጥር ሥራ በትኩረት አለመሥራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመኝታ አጎበር በወቅቱ አለመተካቱ እና ማኅበረሰቡም የተሰጠውን የመኝታ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀም ለወባ በሽታ ሥርጭት መጨመር ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሠብሣቢዋ ሥርጭቱን ለመከላከልም ባለፉት ወራት ጥረቶች መደረጉን ቢገልጹም በሽታው በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨምሩን ነዋሪዎችና የጤና ባለሙያዎች መግለጻቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል። 

ለአብነትም የምግብ ዕጥረት በተከሰተበት ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በ5 ወራት በአማካይ ከሚመረመሩ ህሙማን መካከል 72 በመቶ የሚሆኑት የወባ ታማሚዎች እንደሆኑ መገለጹን ዘገባዎች አመለክተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ ከታህሳስ 23፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ  እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከ7.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን እና ከእነዚህም መካከል 1,157 ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ወባ አሁንም አሳሳቢ የጤና ስጋት ሲሆን 75 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ መሬት እና 69 በመቶ የሚሆነው በነዚህ አከባቢዎች የሚኖረው ህዝብ በተለይም ህጻናት ለከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁሟል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደ ‘አኖፌሌስ ስቴፈንሲ’ የተሰኘ የወባ ትንኝ መስፋፋት፣ ድርቅ፣ የምግብ ዋስትና እጦት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና በሃገሪቱ በቀጠሉት ግጭቶች የተነሳ በኢትዮጵያ ያለው የወባ በሽታ ስጋት ከባድ መሆኑን አመላክቷል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button