
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/ 2017 ዓ/ም፦ “በሁለት ሳምንት ይሄን መንግስት አባርሬ 4ኪሎ የአባቶቼን እርስት እወርሳለሁ ያለው ኃይል አልተሳካለትም” ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ይህን ያሉት ዛሬ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበቅ ወቅት ነው።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል የሆኑት አቶ አበባው ደሣለው በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት እየደረሰ ”ጅምላ እስራትና ከሕግ አግባብ ውጭ ግድያ” እየደረሰ መሆኑን ጋር ገልጸዋል።
አባሉ የመንግስት ኃይሎች የክልሉን ጸጥታ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለመቆጣጠር ዘመቻ ተጀምሮ ነገር ግን ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗል፤ ችግሩ ይበልጥ እየከፋ እንጂ እየተሻሻለ አይደለም ብለዋል።
“ንጹሃን ዜጎች በከባድ መሳሪያ እና በድሮን እየሞቱ ነው” ያሉት አቶ አበባው፤ ሲቪል ተቋማት የሆኑ ጤና ጣቢያዎች ፣ ትምህርት ቤቶች እየወደሙ መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ጥያቄ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ “በ2 ወር እንቆጣጠራለን ብላችሁ ገብታችሁ” የሚለው መታረም ያለበት ነው። ምንድን ነው የምንቆጣጠረው? ከማን ነው የምንቆጣጠረው? ይልቅ በአንጻሩ ያልተሳካው በሁለት ሳምንት ይሄን አረፋ መንግስት አባርሬ 4ኪሎ የአባቶቼን እርስት እወርሳለሁ ያለው አልተሳካለትም። እንጂ እኛ በህጋዊ መንገድ አሸንፈን ነው ክልሉን የተቆጣጠርነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በማብራሪያቸው እርሳቸው የሚመሩት አስተዳደር በአማራ ክልል እየተካሄደ የሚገኘውን ግጭት በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
“ጦርነትን በወሬ ሳይሆን በተግባር እናውቀዋለን፤ ስለዚህ አንፈልገውም።” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም መንግሥታቸው በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን አስታውሰዋል።
ከታጣቂዎች ጋር ንግግር መኖሩን ገልጸው፤ “እንዴት ከዚህ መንግስት ጋር ትነጋገራለህ ብለው የሚወቅሱ ሰዎች አሉ” ብለዋል። በዚህም ሰላም ፈላጊዎቹ ደበቅ ያላሉ ሲሉ አክለዋል።
“ሽማግሌዎች በእምብርክክ እንዲሄዱ ተደርገው ተመልሰዋል” ሲሉ የተደመጡት ጠ/ ሚኒስትሩ፤ አሁንም ንግግሮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንና ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲሰጥ የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ አንስተዋል።
ነገር ግን “ሁሉም ሰው ሰላም ይፈልጋል ማለት አይደለም። ሃገራት መኖሪያ ቤት ይገነባሉ በዛውም ልክ ማረሚያ ቤት ያስፈልጋል።” ሲሉ ተናግረዋል።
“ሃሳብ አልቦ ትግል ምንም አይሰራም።” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አያይዘውም “ከዚህ በፊት በሽፍትነት የሚታወቁ ሰዎች አሁን ተሰባስበው የትጥቅ ታጋዮች ተብለው መጥተዋል” ብለዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና መሩ አስተዳደር የፈጠረውን የኢንዱስትሪ ዓቅም ከዚህ ቀደም መቼም አግኝቶ እንደማያውቅ ገልጸው፤ “የአማራ ክልል ካለማ ኢትዮጵያ አትለማም” በሚል እሳቤ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች በክልሉ እየተካሄዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ክልሉ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የልማት እና የኢንዱስትሪ ማዕከል መደረጉንም ተናግረዋል።
“እኛ አማራ ክልል ላይ ልማት ነው እያመጣን ያለነው።” ሲሉ የገለጹት ጠ/ሚ ዓብይ ሆኖም ልማት እያደናቀፈ ያለው “የዛው አከባቢ ሰው” ነው ሲሉ አመላክተዋል።
የጋዜጠኞችን፣ የአንቂዎችን እንዲሁም የፖለቲከኞችን እስር በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄም “አንዳንድ ሠዎች እዚህም ሰላም ውስጥ እዛም ጦርነት ውስጥ አሉ። አንድ እግር በሲኦል አንድ እግር በገነት አርጎ መኖር አይቻልም። ወይ ከሲኦል እሳት ወይ ከገነት ፍሬ ተቋዳሽ መሆን ይገባል።” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። አስ