
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7/2017 ዓ/ም፦ ከ230 በላይ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ከቋሚ ስራቸው ተፈናቅለው የጉልበት ስራ እንዲሰሩ እየተደረጉ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ አንድ የፋብሪካው ሰራተኛ በፋብሪካው ከ13 ዓመታት በላይ መስራታቸውን ገልጸው ቋሚ ሰራተኛ ሆነው በ2013 ዓ.ም መመደባቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
ሆኖም ከአንድ ወር በፊት አዲስ መዋቅር ተሰርቶ እሳቸውና ሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው ወደ ጉልበት ስራ እንዲገቡ የሚገልጽ ማስታወቂያ መለጠፉን ተናግረዋል።
“አብዛኞቻችን ለዘጠኝ አመታት የቀን ስራ ነበረ የሰራነው። ከዛ ቋሚ አድርገውን ስንሰራ ከቆየን በኋላ ድርጅቱ አደጋ ውስጥ ስለገባ እናንተ ከደረጃ ሰባት በታች ያላችሁ አመራሮች ድርጅቱን መታደግ ከፈለጋችሁ ወርዳችሁ የቀን ስራ እየሰራችሁ መቆየት መቻል አለባችሁ አሉን።” ያሉት እኚሁ የፋብሪካ ሰራተኛ አክለውም ከዚህ በፊት በደረጃ 4 የስራ መደብ የ5ሺህ ብር ደመወዝተኛ እንደነበሩ እና አሁን በተሰራው አዲስ መዋቅር ገቢያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል ስጋታቸውን አጋርተዋል።
“አሁን ሊሆን የሚችለው በጣም ብለፋ እንኳን 2500 ነው በወር የሚደርሰኝ በአሁኑ። የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ። ሁለት ልጆች አሉኝ። ደግሞ ከጎን የምታግዛቸው እህት ወንድም አሉ። እናት አባት አሉኝ። እነሱ እያሉ ነው እንግዲህ ከ5000 ብር ደመወዝተኛ ወደ 2500 ብር እንድወርድ የተደረገው”ብለዋል።
አያይዘውም ከደረጃ ሰባት በታች ያሉ በትንሹ 186 ሰራተኞች ከደረጃቸው ዝቅ ብለው የጉልበት ስራ እንዲሰሩ መደረጋቸውንና ሌሎች 106 የሚሆኑት ደግሞ ምንም የስራ መደብም ሆነ የስድስት ወር ደመወዝ ያልተከፈላቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሌላኛው አቶ አየነ ካሳ (ስማቸው የተቀየረ) የተባሉ የፋብሪካው ሰራተኛ በበኩላቸው ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በፋብሪካው የሚሰሩ እና የስራ መደባቸው ከደረጃ ሰባት በላይ የሆኑ ሰራተኞች ወደ ኦሞ ኩራዝ፣ መተሀራ እና ወንጂ ስኳር ፋብሪካ መዘዋወራቸውን ገልጸው ከደረጃ ሰባት በታች የሆኑ ሰራተኞችን ግን ቋሚ የስራ ውላቸው ተቋርጦ የጉልበት ስራ እንዲሰሩ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
“236 ሰራተኞች ነን አጠቃላይ። ቋሚ ሆነን ከ11 ዓመታት በላይ ለፋብሪካው ስናገለግል ቆይተን አሁን የጉልበት ስራ በሰራህበት ልክ ይከፈልሃል ብለው ደብዳቤ ጽፈው ለጥፈዋል።አገዳ መቁረጥ አይነት ስራዎች ማለት ነው። እኔ ከዚህ በፊት ንብረት ክፍል ውስጥ ነበረ የምሰራው። ከእኔ ጋራ አብረው ሲሰሩ የነበሩ ጓደኞቼም ሹፌር እና ጥበቃ ሰራተኛ ነበሩ።” ያሉት አቶ አየነ አክለውም አሁን ላይ በቀን በሰሩት መጠን እንደሚከፈላቸው ጠቁመዋል።
“ቀኑን ሙሉ ስትሰራ ከዋልክ አምስት ብርም አስር ብርም ሊሆን ይችላል የሚከፈልህ። በሰራህበት ልክ ነው የሚከፈልህ። አገዳ ስትቆርጥ ውለህ ሜትር ተለክቶ ነው ሚከፈልህ። በሜትር 36 ሳንቲም አለ ለምሳሌ አገዳ ቆረጣ። ያም እንግዲህ ቆርጠህ ወደ ተዘጋጀልህ ቦታ ደርድረህ ነው የሚከፈልህ።” ሲሉ ስለሁኔታው አስረድተዋል።
ከዚህ በፊት በወር 6698 ብር የተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ ሲያገኙ እንደቆዩ የገለጹት አቶ አየነ አሁን ከደረጃቸው ዝቅ ብለው እንዲሰሩ በመደረጋቸው ገቢያቸውን ሊቀንሰው እንደሚችል ይገልጻሉ።
“አሁን በቀን ስራህ ስለሆነ የሚታሰበው በወር ለፍተህም 1000 ብር ብቻ ልትሰራ ትችላለህ። ሁለት ልጆች እና አንዲት የቤት እመቤት የሆነች ሚስት አለችኝ። ይሄ ብር ደግሞ ቤተሰብን ቀርቶ ራስህን ማስተዳደር አይችልም።” ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላኛው ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የፋብሪካው ሰራተኛ በበኩላቸው ፋብሪካው ከደረጃ ሰባት በታች ያሉ ሰራተኞችን የሥራ ውል በማቋረጥ ወደ ጉልበት ሥራ እንዲገቡ የሚገልጽ ማስታወቂያ ከነስም ዝርዝራቸው መለጠፉን አረጋግጠዋል።
አክለውም እነዚህ ሰራተኞች የአከባቢው ማኅበረሰብ ልጆች መሆናቸውን ገልጸው፤ ፋብሪካው ከእነዚሁ ሰዎች መሬታቸውን ወስዶ ሁሉም ተስፋ አድርጎ ካበቃ በኋላ ይሄ መፈጠሩ ቅሬታ አስከትሏል ብለዋል።
“ቋሚ ሰራተኞች ነበርን። ፋብሪካው ከሥራ ማሰናበት እንኳን ቢፈልግ ቢያንስ ጥቅማ ጥቅም ሰጥቶ ማሰናበት እንጂ በራሱ ውሉን አቋርጦ ወደ ቀን ስራ ግቡ ማለት አግባብ አይደለም የሚል ቅሬታ ነው ያለን።” ሲሉ ተናግረዋል።
አያይዘውም ፋብሪካው የተወሰኑ ሰራተኞችን ወደ ሌሎች ፋብሪካዎች ማዘዋወሩን ጠቅሰው ይሁን እንጂ 106 የሚሆኑ ሰራተኞች የአምስት ወር ደመወዛቸው እንዳልተከፈላቸው እና የሥራ ምደባም እንዳልተደረገላቸው አብራርተዋል።
በተጨማሪም አሁን ላይ ፋብሪካው ምርት እያመረተ አለመሆኑን ገልጸው ይህም በመብራት ችግር የተነሳ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ አዲስ ስታንዳርድ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ የሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር የሆኑትን ማሩ ተፈራን እንዲሁም የፋብሪካ የሰው ሀብት አስተዳደር ቡድን መሪ የሆኑትን ዓለሙ ፈረደን ለማግኘት በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ላይ ቢደውልም ስለማይነሳ ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡
ይሁን እንጂ ፋብሪካው ከወራት በፊት ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በማህበራዊ ድረገጹ ባስተላለፈው መልእክት ለስራ ማስኬጃ በቂ በጀት ባለመመደቡ፣ የቁንዝላ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ትራንስፎርመር ብልሽት ከሁለት አመት በላይ አለመጠገን እና በሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በ2016 ዓ.ም ስኳር ማምረት አለመቻሉን አስታውቋል፡፡
በዚህ ምክንያት በተፈጠረው የገንዘብ እጥረትም ፋብሪካው ለሰራተኛ ደመወዝ መክፈል ባለመቻሉ ከ15,655 በላይ ሰራተኛ እና የሰራተኛ ቤተሰብ ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን ጠቁሟል፡፡
በአማራ ክልል በአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።
በቻይናው ሲ ኤ ኤም ሲ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ በ95 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው ፋብሪካው በቀን 12 ሺህ ቶን የሸንኮራ አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው ሲሆን እስከ 12 ሺህ ኩንታል ስኳር ማምረት ይችላል። ፋብሪካው ከ15,000 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞችም የስራ እድል ፈጥሯል።አስ