አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24/ 2017 ዓ/ም፦ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ከሰሞኑን በተደጋጋሚ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በርካታ ሰዎች አከባቢያቸውን ለቀው አጎራባች ወደሆኑ ስፍራዎች እየሸሹ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
ከሰሞኑ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለሳ ወረዳዎች በተደጋጋሚ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ከ30 በላይ ቤቶች መፍረሳቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ነዋሪ በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።
መሬት መንቀጥቀጡ በብዛት ያለውና ጉዳት ያደረሰው ስኳር ፋብሪካ በሚገኝበት ዱለሳ ወረዳ ሰገንቶ ቀበሌ ላይ ነው ያሉት ነዋሪው፤ በተጨማሪም አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ላይ በስፋት እየተከሰተ መሆንና ቤቶች ቀን በቀን እየፈረሱ መሆናቸውን ተልጸዋል።
አክለውም በርካታ ቤቶች መፍረሳቸውን፣ በአከባቢው የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማጋጠሙን ተናግረዋል።
ለአብነትም በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ የሚገኘው ኡንጋይቱ ት/ቤት ላይ ከፍተኛ ጉደት በመድረሱ የተነሳ ከትናንት ጀምሮ የመማር ማስተማር ሂደት መቋረጡን አመልክተዋል።
“ከዚህ ቀደም ተመሣሣይ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም ሲስተዋሉ ነበር” ያሉት ነዋሪ አክለውም በወቅቱ ተነካክተው ዘመም ብለው የነበሩ ቤቶች አሁን ላይ ከሰሞኑ እንደአዲስ ባገረሸው የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ምክንያት ሙሉ በሙሉ በመፍረስ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት በአከባቢው በተፈጠረ ስጋት የተነሳ በርካታ ሰዎች በተለይም ከዱለሳ ወረዳ ከሰም ስኳር ፋብሪካ አከባቢ ተነስተው ወደ አጎራባች ወደ ሆኑ አከባቢዎች በመሸሽ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
“ስኳር ፋብሪካው አከባቢ ያሉ ሰዎች ሙሉ በሙሉ አከባቢያቸውን ለቀው ወጥተዋል። ቤቶች ፈርሰዋል። ሰውም እቃውን ይዞ እየተሰደደ ነው ወደ አዋሽ አርባ። ብር ያለው በመኪና ይወጣል የሌለው በእግሩ በጫካም አድርጎ እየሸሸ ነው። የገጠሩ ማህበረሰብ ደግሞ እቃውን በግመል እየጫነ ከብቱን እየነዳ እየወጣ ነው። በጣም ችግር ውስጥ ነን ያለነው። አፋር ክልል ዞን ሶስት ፈንታሌ እና ዱለሳ ወረዳ በጠቅላላ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው ያለው።” ብለዋል።
በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት አስፋልት ሲሰነጠቅ ማየታቸውን ገልጸው አሁን ላይ ስንጣቂው እየሰፋ መምጣቱን እና ከሰዎች መኖሪያ ቤት ውስጥ ሳይቀር ውሃ ሲፈልቅ ማየታቸውን ጠቁመዋል።
ሌላኛው ኡስማን አብዲ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ተመሣሣይ ክስተቶች ከሶስት ወራት በፊት መከሰታቸውን አንስተው አሁን ላይ በድጋሚ የመሬት መንቀጥቀጡ ሳቡሬ፣ ቦሊቃ፣ ቀበና እና አርብሃራ በተሰኙ አከባቢዎች በስፋት መከሰቱን ገልጸዋል።
“በተለይም በአርብሃራ እና ቦሊቃ መካከል የተሰነጠቀው አስፋልት ጥልቀቱ በጣም ትልቅ ነው” ብለዋል።
አያይዘውም በዱለሳ ወረዳ የሚኖረው አብዘሃኛው አርብቶ አደር የማህበረሰብ ክፍል ወደ አዋሻ ሰባት እና አርጎባ እየሸሸ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም “በአዋሽ ፈንታሌ ሀራሜ በተሰኘው ስፍራ የሚገኘው የከሰም ግድብ ሊደረመስ ነው የሚል ወሬ በአከባቢው በመሰራጨቱ ምክንያት ባለፈው እሁድ ታህሳስ 19 ሌሊቱን ብዙ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሸሽተዋል” ብለዋል።
አክለውም የሚመለከተው አካል ለአከባቢው የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ሌላኛው ስማቸውን እንዳንጠቀስ የጠየቁ በአዋሽ ሰባት ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት “ከፍተኛ ስጋት አለባት” ብለው ከገለጿት እና በአዋሽ ፈንታሌ ከምትገኘው የዱሃ ቀበሌ በርካታ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው 43 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው አዋሽ ሰባት አከባቢ በመምጣት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
“በርካታ ሰዎች ናቸው በመግባት ላይ ያሉት። አቅም ያለው ቤት ተከራይቶ ገብቷል። ሌላው ደግሞ ከዘመድ ጋር ተጠግቶ ነው ያለው። ሸሽተው ሲመጡም አብዘሀኞቹ ከልጆቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው በቀር ይዘው የመጡት ንብረት የለም” ሲሉ ስለ ሁኔታው ያዩትን አብራርተዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገራቸው የአዋሻ ፈንታሌ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አደን በለአ በበኩላቸው የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ ከዚህ ቀደም በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም በስፋት ሲታይ እንደነበረ ገልጸው አሁን ላይ ክስተቱ እንደአዲስ ማገርሸቱን ተናግረዋል።
አክለውም በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ የሚገኘው የኡንጋይቱ መጀመርያ ደረጃ ት/ቤት ላይ ጉዳት መድረሱንና ትምህርት መቋረጡን አረጋግጠዋል። በተጨማሪም በዱሃ ቀበሌ የሚገኝ መስጂድ ላይ መሰነጣጠቅ አጋጥሟል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከሴቶችና ህጻናት፣ ከግብርና እና ከጸጥታ ጽ/ቤቶች የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን ተዋቅሮ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
እንዲሁም በአከባቢው ከሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በስጋት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ተሻለ ቦታ የማዘዋወር ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከክልሉ እና ከፌደራል የአደጋ መከላከል ኮሚሽኖች ጋር በመናበብ የተቀናጀ ስራ እየተሠራ እንደሚገኝ አበክረዋል።
ሰኞ ታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በተለይም በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ ንዘረታቸው እስከ አዲስ አበባ የተሰሙ ከ10 በላይ የተመዘገቡ የመሬት መንቀጥቀጦች መከሰታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ሁኔታውን በተመለከተ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ የርዕደ መሬት መመዝገቢያ መረብ ኃላፊ የሆኑት ፕ/ር አታላይ አየለ በበኩላቸው “መደናገጥ አያስፈገልግም” ብለዋል።
ፕ/ር አታላይ ሰሞነኛ ክስተቶች “መካከለኛ” ደረጃ የሚሰጣቸው ርዕደ መሬቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ርዕደ መሬቶቹ የሚከሰቱባቸው ስፍራዎች ግን የጉዳት ደረጃቸውን እንደሚወስኑት መግለጻቸውን ከጣቢያው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
“ጉዳት ለማድረስ መሀል ከተማ ከተፈጠረ 3.0 ሬክተር ስኬል ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። የተፈጠረበት ቦታ የት ነው? የሚለው እንጂ አሁን የተፈጠረው ከፍተኛ ነው የሚባል አይደለም” ሲሉ አብራርተዋል።
ቀጠል አድርገው በኢትዮጵያ የርዕደ መሬት ክስተት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ሲናገሩም፤ “ከዚህ ከፍ ሊል የሚችልበትም እድል ይኖራል፤ እየቀነሰ ሊሄድም ይችላል። በቅርብ ጊዜ ግን የሚያቋርጥ አይመስልም” ብለዋል።
“ንዝረቱም እስከ አዲስ አበባ ድረስ ሊሰማ ይችላል። ግን በጉዳት ደረጃ እስካሁን የተመዘገበ የለም። ወደፊትም በ160 ኪ.ሜ በላይ ሄዶ ጉዳት ያደርሳል ብለን አንጠብቅም። ብዙ መደናገጥ አያስፈልግም ብለዋል። አስ