ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ መጅሊሱ በአክሱም ከተማ ሂጃብ መከልከሉን በተመለከተ “ምንም እልባት” አለመገኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24/ 2017 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ትምህርት እንዳይከታተሉ መከልከሉን በተመለከተ ምንም እልባት አለመገኘቱን አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ “የአክሱም ከተማ ትምህርት ቢሮ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሙስሊም ሴት ተማሪዎችን የእምነት አለባበስ አስመልክቶ ትምህርታቸውን በሚጎዳ መልኩ ከአንድ ወር ባላነሰ ጊዜ ከትምህርት ገበታቸው እንዲስተጓጎሉ ከማድረጉም ባሻገር አንዳንድ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው መታሰራቸውን” ገልጿል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት፤ ከትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ጋር እየተነጋገረ መቆየቱን ገልጾ “ምንም እልባት አለመኖሩን በተግባር መረዳት ችለናል” ብሏል፡፡

በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አክሱም ከተማ “በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሂጃብ እንዳይለብሱ” መከልከላቸውን የገለጹ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ድርጊቱ “የትምህርት እና የሀይማኖት ነጻነታችንን ይጋፋል” ሲሉ ተቃውመዋል

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ የሆኑት ሃጂ መሀመድ ካህሳይ የትምህርት ቤቶቹን ተግባር በመተቸት በተለይ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ በመከልከላቸው የተነሳ ለብሔራዊ ፈተና አለመመዝገባቸውን አረጋግጠዋል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ታህሳስ 9 በጻፈው ደብዳቤ ከአክሱም ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት ቅሬታ መቀበሉን ገልጿል። አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች መደበኛ አሰራሮችን ቢከተሉም አንድ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገደቦችን እንዳስቀመጠ ገልጿል።

ቢሮው “ከቢሮአችን ከተላኩ ባለሙያዎች ጋር በመወያየት ጉዳዩን እንዴት መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል።” ሲል ገልጿል። ይሁን እንጂ ቢሮው አክሎ፣ “ጉዳዩን ለመፍታት ስምምነት ቢደረስም፣ ከጊዜ በኋላ ከትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላላ ምክር ቤት ጉዳዩ ያልተፈታ መሆኑን በመግለጽ ቅሬታ አቅርቧል” ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮው አክሎም አዲስ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስ ተጨማሪ ገደቦች ወይም መስፈርቶች መጣል እንደሌለባቸው እና የቀድሞው የአለባበስ ስርዓት በሥራ ላይ መቆየት እንዳለበት አፅንዖት ሰጥቷል።.

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በመግለጫው፤ የአክሱም ከተማ ሙስሊም ነዋሪዎች “ለዘመናት የነበረባቸውን የእምነት ነፃነት፣ የመስገጃ ቦታ ችግርና የቀብር ቦታ ችግር እልባት ያልተሰጠበትና ወደ ባሰ ሁኔታ እየሄደ ነው” ሲል ገልጿል።

“የክልሉና የፌዴራል መንግስት የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤቶች በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግጋትና በህገ መንግስቱ አንቀጽ 27 መሠረት በዚህ ዘመን በጋራ እምነቶች ተከባብረው በሚኖሩበት አገር እሴቱን የሚሸረሽር ተግባር መፈፀሙን በጥብቅ እናወግዛለን” ብሏል።

የሙስሊም ማህበረሰብ መብቶች ሳይሸራርፉ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደገግና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ይህንኑ እንዲያስፈጽሙ የጠየቀው መግለጫው ይህንን ድርጊት በፈፀሙ “ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እዲወሰድ” ጠይቋል።

መጅሊሱ “የሙስሊም ማህበረሰብና ሌሎች የእምነት ተቋማትና ተከታዮች ጉዳዩን እንዲያወግዙና ከአክሱም ሙስሊም ማህበረሰብ ጎን እንዲቆሙም” ጥሪ አቅርቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button