ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “የፕሪቶሪያ ስምምነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀዳሚ ተግባር የተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው መመለስ መሆን አለበት” - በትግራይ ጉብኝት ያካሄዱ ዲፕሎማቶች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6/2017 ዓ.ም፡- ትላንት የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በትግራይ ጉብኝት ያካሄዱት የአውሮፓ እና የአሜሪካ ልዑካን የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አስታወቁ።

የአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና የአውሮፓ ህብረት ልዑካን ትላንት የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም መቀለ በመገኘት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ከሚመራው ህወሓት አመራሮች ጋር በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ዙሪያ መክረዋል፤ በመቀለ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮችንም ጎብኝተዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከልዑክ ቡድኑ ጋር በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት አተገባበር እና በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ መወያየታቸውን በይፋዊ የኤክስ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

“የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀዳሚ ተግባር የተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው መመለስ መሆን እንዳለበት ዲፕሎማቶቹ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፤ የሚቻላቸውን ሁሉንም ለማድረግ ቃል ገብተዋል” ብለዋል።

የትግራይ የፖለቲካ ሁኔታ መበላሸት ዋነኛ ምክንያት በዋናነት የጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የፌደራል መንግስት እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት የክልሉ ተፈናቃዮች በወቅቱ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ባለመድረጋቸው የመጣ ነው የሚለውን ጉዳይ ሁላችንም ተስማምተንበታል ብለዋል።

የትግራይ ፖለቲካ ሀይሎች በስልጣን ሽኩቻ እና በተራ ጉዳዮች ዙሪያ ከመነታረክ ይልቅ ዋነኛ ትኩረታቸው ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በማስመለስ ዙሪያ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውንም አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል።

ተፈናቃዮቹ ያልተተገበረው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በሰማይ ላይ እንዳለ ደመና ሁኖብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ጉብኝቱን ያካሄዱት የአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና የአውሮፓ ህብረት ልዑካኑ በመቀለ ከተማ ተፈናቃዮች ተጠልለውባቸው በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎችን በመገኘት ከተፈናቃዮች ጋር መወያየታቸውን ከትግራይ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ተፈናቃዮችን ካነጋገረው ልዑክ ቡድን አንዱ የሆኑት በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዊልች የጉብኝቱ ዋና አላማ በትግራይ ያለውን የሰላም ሁኔታ ለመታዘብ እና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ነው ብለዋል።

በዚህም አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዳልረሳችሁ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን ሲሉ ተናግረዋል።

የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ መጎብኘታቸውን የገለጹት በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክስ ላሚክ “ፈረንሳይ እንደ ሀገር ከፌደራል መንግስት ጋር ያላትን ግንኙነት የፕሪቶሪያን ስምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ ትጥራለች ብለዋል።

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተወካዮች ባለፉት አራት አመታት ድምጻችንን ሰምተው ከመሄድ ያለፈ ያስገኙልን መፍትሄ የለም ሲሉ ቅሬታቸውነ አሰምተዋል፤ አሁንም የምንጠይቀው በተግባር ይገለጽልን የሚል ነው ብለዋል።

የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት የፈረሙት አካላትም ይሁን አለምአቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቅባቸውን ባለመወጣታቸው ተፈናቃዮች በረሃብ ና በህመም እየሞቱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሰላም ስምምነቱ ምክንያት ወደ ቀያቸው ተመልሰው የነበሩ የተወሰኑ የጸለምት ተፈናቃዮች የደህንነት ዋስትናቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲመለሱ ባለመደረጉ ለሞት ተዳርገዋል እንደገናም የተፈናቀሉ አሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የበጀት እጥረት አጋጥሞናል በሚል ለጋሽ ድርጅቶች ስራቸውን አቋርጠዋል፤ በዚህም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንገኛለን ወጣቶቻችንም እየተሰደዱ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

“ስለዚህ በመሬታችን ላይ ሰርተን እንድንበላ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የደህንነት ዋስትናችን በተጠበቀ መልኩ ወደ ቤታችን በሰላም እንድትመልሱን እንፈልጋለን” ሲሉ ጠይቀዋል።

አባሳደሮቹ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በተጨማሪ በደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ከሚመራው የህወሓት ቡድን ጋር መወያየታቸውንም ከፓርቲው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ልዑክ ቡድኑ ከደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ከምክትላቸው አማኑኤል አሰፋ እና ከጽ/ቤት ሀላፊዋ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር ጋር በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አተገባበር እና ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች በሚገኘየ የክልሉ ነዋሪዎች ዙሪያ መወያየታቸውን መረጃው አመላክቷል።

ባለስልጣናቱ ለልዑክ ቡድኑ “የፕሪቶሪያ ስምምነት መተግበር ለክልሉ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ ስምምነቱ ተግባራዊ ባለመሆኑ ህዝቡ በስደተኛ ካምፖች ውስጥ በረሃብና በበሽታ እየሞተ ነው” ሲሉ መግለጻቸውንም መረጃው አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button