ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ መንግሥት በዳኢዶ መጠለያ ጣቢያ ያሰፈራቸውን ተፈናቃዮች ዳግም ወደ ስፍራ ለማዘዋወር “በሽምግልና” ጭምር ቢሞክርም አርብቶአደሮች ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2017ዓ.ም፦ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በተደጋጋሚ የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ተከትሎ አከባቢያቸውን ለቀው አሚበራ ወረዳ በሚገኘው ዳኢዶ መጠለያ ተጠልለው የሚገኙ አርብቶአደሮችን መንግሥት ዳግም ወደ ሌላ ስፍራ ለማዘዋወር በሽምግልና ጭምር ቢጠይቅም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተገለጸ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት ያቋቋመው ኮማንድ ፖስት በዳኢዶ መጠለያ ተጠልለው የሚገኙ አርብቶ አደሮችን አዲስ ወዳዘጋጀው እና በአዋሽ አርባ በሚገኘው ‘አዲስ ራዕይ’ ወደተሰኘ መጠለያ ጣቢያ ለማዘዋወር ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።

“ከክልሉ ኮማንድ ፖስት እና የሀገር ሽማግሌዎች ተወጣጡ ሰዎች ባሳለፍነው ሳምንት መጥተው አወያይተውን ነበር። አከባቢው አሁንም የአደጋ ስጋት ስላለበት አዋሽ አርባ በሚገኘው አዲስ ራዕይ መጠለያ እንድንዘዋወር ጠየቁን” ያሉት ነዋሪው ሆኖም አሁን ተዘጋጅቷል የተባለው ስፍራ ለኑሮ ምቹ አለመሆኑን በመጥቀስ አርብቶ አደሩ ለመዘዋወር ፈቃደኛ አልሆነም ብለዋል።

በተጨማሪም “አሁን ባለንበት ዳኢዶ አዋሽ ወንዝ ያቋርጣል። ብዙ ፍልውሃዎች አሉ። ለከብቶቶቻችንም የሚሆን ቦታ ነው። የሚጠቱት ውሃም ሆነ የሚመገቡት ነገር አለ።” ሲሉ ገልጸው ያለንበት ቦታ ዳግም ለመሬት መንቀጥቀጥ ስጋት ቀጠና ተደርጎ ወደ አዲስ ራዕይ የተባለ አዋሽ አርባ የሚገኝ መጠለያ እንድንሄድ ነው የተጠየቅነው ብለዋል። አክለውም ወደ አዲሱ መጠለያ ለመሄድ ለከብቶቹ የሚሆን “ወንዝ የሌለበት በረሃ” በመሆኑ ወደዛ ለመዘዋወር ፍቃደኛ አለመሆናቸውን አስረድተዋል።

ከአዲስ ስታንዳንድ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሌላኛው አርብቶ አደር ነዋሪ በበኩላቸው፤ አሁን እንዲሰፍሩ የጠየቁትን አከባቢ (አዲስ ራዕይ መጠለያ ጣቢያ) ከዚህ በፊት እንስሳት ሲያረቡ እንደሚያውቁት ገልጸው ቦታው “ምንም የሌለበት አስቸጋሪ” ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።

“አዲስ ራዕይ ማለት ከአዋሽ አርባ ዝቅ ብለህ የሚገኝ ነው። ከከተማ ራቅ ይላል። ውሃ የለም። በአከባቢው ዛፍ እንኳን ስለማታገኝ ለመጠለያ እና ለምግብ ማብሰያ የሚሆን እንጨት እንኳን ማግኘት አዳጋች ቦታ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።   

በዚህም ምክንያት መንግሥት በአከባቢው የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን ለማዘዋወር በሽምግልና ሳይቀር ቢሞክረም ነዋሪው ባለመስማማቱ አሁንም በዳኢዶ መጠለያ ጣቢያ በርካታ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ተነሱ ከተባልን ሁለት ሳምንት ይሆነናል። ነዋሪው ሳይስማማ ሲቀር ባለፈው ሳምንት በሽምግልና ተሞከረ። እነሱ የሚሉን አንደኛ አሁን የምንገኝበት ዳኢዶ መጠለያ ጣቢያ ለመሬት መንቀጥቀጥ አስጊ ነው፣ በተጨማሪ ደግሞ ከመንገድ ዳር ያለ ቦታ ስለሆነ ለመኪና አደጋ ተጋላጮች ናችሁ ነው የሚሉት” ያሉት ነዋሪው ሆኖም ውሃን ጨምሮ ያለ በቂ መሰረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦት መኖር አንችልም ብለን ወደተባለው ቦታ ከመሄድ ታቅበናል ብለዋል።

“አዲስ ከተዘጋጀልን ቦታ ወደ ከተማ ለመሄድ ብንፈልግ እንኳን ባጃጅ ወይም የሞተር ትራንስፖርት ነው መጠቀም የምትችለው እሱ ደግሞ ለደርሶ መልስ 1000 ብር ድረስ መክፈል ይጠበቅብናል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ጥሪውን ተቀብለው አዲስ ወደተዘጋጀው አዲስ ራዕይ የመጠለያ ጣቢያ የተዘዋወሩ የተወሰኑ ነዋሪዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

እኚሁ ነዋሪ ከባለፈው ሳምንት ሽምግልና በኋላ ወደ ዳኢዶ መጠለያ ጣቢያ ሲሰጥ የነበረው የምግብ እርዳታ በመቀነሱ ምክንያት ነዋሪው ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን አክለዋል።

“ምንም ነገር አልመጣልንም ተነሱ ከተባልን በኋላ። አቅርቦቱ ቀንሷል። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በአፋር እና በኦሮሚያ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች መከሰታቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፤ “በአዋሽ እና ዱሌቻ ወረዳዎች ያሉ የተወሰኑ ነዋሪዎች በተለይም  ከብቶቻቸው እና ንብረታቸው ላይ ስጋት ያላቸው የአርብቶአድር ማህበረሰቦች ወደ ሌላ ቦታ ለመዘዋወር ፈቃደኞች አይደሉም” ሲል መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት መሠረት፤ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አደጋ ካለባቸው አካባቢዎች ለማስወጣት አስገዳጅ እርምጃዎችን ለመውሰድ እያሰበ መሆኑን ገልጾ ነበር። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button