ህግ እና ፍትህዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ አቶ ታዬ ከእስር ቤት በር ላይ ተይዘው ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሀዳር 26/ 2017 ዓ/ም፦ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንዳኣ በዋስትና ከእስር እንዲፈቱ መወሰኑን ተከትሎ ትናንት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በመውጣት ላይ እያሉ በመንግስት ጸጥታ ኃይሎት ከበር ላይ ተይዘው ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።

ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ዛሬ ጠዋት ወደ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አምርተው ከታዬ ደንዳኣን ጋር መገናኘታቸውን ገልጸዋል። “ወደዛ እንደወሰዷቸው ሰምተን ዛሬ ጠዋት ሄደን ነበር፤ ዛሬ አግኝተነው ወጥተናል፤ ቀጥሎ የሚሆነውን እንጠብቃለን” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

ታዬ ህዳር 23 ቀን በዋለው ችሎት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በዋስትና እንዲፈቱ መወሰኑን ተከትሎ ትላንት ህዳር 25፣ 2016 ዓ/ም ከእስር ቤት እንደተለቀቁ ከበር ላይ “ምስክ ባደረጉ” ሰዎች መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ተናግረዋል።

“ተለቋል ማለት አይቻልም፤ ከቤተሰቦቹ ጋር አልተገናኘም፤ እራሳቸው ናቸው ገብተው የወሰዱት፤ ከሰዓት 11 ሰዓት አካባቢ ከእስር ቤት ሊወጣ ሲል ቤተሰብ ሳያየው ትፈለጋለህ በለው ወስደውት ሄዱ። ከበላይ አካል የተጻፈ ያሉትን ደብዳቤ ይዘው ነበር። ምን እንደሆነ ግን አላነበብንም” ብለዋል።

የጸጥታ ኃይሎቹን ብዛት እንደማያውቁ የገለጹት ወ/ሮ ስንታየሁ፤ “የሲቪል ልብስ የለበሱ እና ማስክ ያደረጉ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ ደምብ ልብስ የለበሱ አካላት ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ በሁለት ፓትሮል ተሽከርካሪ ቂሊንጦ አካባቢ ሲዘዋወሩ እንደነበር ሰምተናል” ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

አቶ ታዬ ፍርድ ቤቱ በዋስትና እንዲለቀቁ ከወሰነላቸው በኋላ ለሁለት ቀናት እስር ቤት ማሳለፋቸውን የገለጹት ወ/ሮ ስንታየሁ፤ ይህም የሆነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ላይ የቀን ስህተት በመኖሩ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። “የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ይህን ነገር እየጠበቀ የነበረ ይመስላል። ጥቃቅን ምክንያቶችን ሲደረድሩ ነበር” ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደኣ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ታህሳስ 2 ቀን በጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አቶ ታዬ ደንደኣ  ታኅሣስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋሉት  “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር  ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰሩ ስለተደረሰባቸው” በሚል መሆኑን የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል በወቅቱ አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎም የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ታዬ ደንደአ ላይ ሶስት ክሶችን አቅርቧል።

በዚህም መሰረት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው፤ “ተከሳሹ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስትንና የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው  ፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ የፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ድጋፍ የሚገልጹ መልዕክቶችን  ሲያስተላልፉ ነበር” የሚል ነው፡፡

እንዲሁም ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም  ከረፋዱ 5 ሰዓት  ላይ በልደታ ክ/ከ ወረዳ 6  በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽን ኮቭ  መሳሪያ ከ2 ክላሽ ካዝና  እና ከ60 ጥይት ጋር ይዘው መገኘታቸው ተጠቅሶ ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሐምሌ 30 በዋለው ችሎት ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ነጻ የተባሉ ሲሆን የጦር መሳሪያ ወንጀሎችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ሶስተኛው ክስ እንዲከላከሉ ብይን መሰጠቱም ይታወሳል፡፡

አቶ ታዬ ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉ አምስት የመንግሥት ባለስልጣናትን ለምስክርነት ጠርተው የነበር ሲሆን በምስክርነት ካቀረቧቸው መካከል በቅርቡ ከኃላፊነት የተነሱት የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም እና የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ምስክርነታቸውን መስጠታቸው ይታወሳል።

አቶ ታዬ በምስክርነት ቀርበው ያስረዱልኝ ካሏቸው መካከል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚገኙ ሶሆን ምስክርነታቸውን ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 3/ 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button