ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ የኤች አይ ቪ ስርጭት በእጥፍ መጨመሩን ጥናት አመለከተ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 26/ 2017 ዓ/ም፦ በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ የኤች አይ ቪ ስርጭት በእጥፍ መጨመሩን የትግራይ ጤና ምርምር ኢንስቲትዩት በቅርቡ ባደረገው ጥናት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በትግራይ ክልል የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት መጨመሩን ጠቁሞ ይህም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው 1.4 በመቶ፤ ከጦርነቱ በኋላ ወደ 3 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጿል።

በ30 ወረዳዎች ውስጥ የተካሄደው ጥናቱ ተጋላጭ በሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች፣ በተፈናቃዮች ግለሰቦች እንዲሁም በወሲብ ንግድ በተሰማሩ ሴቶች ላይ ከፍተኛ የስርጭት መጠን መታየቱን አመላክቷል።

በዚህም መሰረት 5.5 በመቶ የሚሆነው የበሽታው ስርጭት በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዲሁም 8.5 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በወሲብ ንግድ ላይ በተሰማሩ ሴቶች ላይ መመዝገቡን ጠቁሟል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ጸጋይ ሃድጉ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ምዕራብ ትግራይን ያላካተተው ጥናቱ የኤች አይ ቪ እና ሌሎች ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ስርጭትን በመለየት የክልሉን የጤና ተግዳሮቶችን በተመለከተ ጠቃሚ ግንዛቤዎችን ይሰጣል።

በተለይም እንደ ራያ አዘቦ፣ ክልተ አውላዕሎ እና ሀውዜን ባሉ ወረዳዎች የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በገጠር አካባቢዎች የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ ጸጋይ አክለውም ጦርነቱ የክልሉን የጤና ጥበቃ ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ ማስተጓጎሉን እና እንደ ኤች አይ ቪ ምርመራ፣ የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ህክምና  እንዲሁም በደም ውስጥ ያለውን የቫይረስ መጠን ክትትልን የመሳሰሉ ቁልፍ አገልግሎቶች ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረ አብራርተዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም መፈናቀል፣ የምግብ ዋስትና እጦት እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ለቫይረሱ መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል።

“የጥናቱ ግኝቶች በትግራይ የኤች አይ ቪ መከላከል፣ የምርመራ እና ህክምና አገልግሎትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ያመላክታሉ” ሲሉ አቶ ፀጋይ ለአዲስ ስታንዳርድ አክለው ገልጸዋል።

እ.ኤ.አ በ2022 በመላ ኢትዮጵያ የነበረው የቫይረሱ ስርጭት ወደ 0.93 በመቶ ቢቀንስም፣ የፀረ-ኤች አይ ቪ መድኃኒቶች፣ የመመርመሪያ ቁሳቁሶች እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች እጥረት ምክንያት በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የጤና ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል በማሳተፍ ውጤታማ የመከላከልና የቁጥጥር ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ባሳለፍነው ዓመት 2016 ዓ.ም ግንቦት ወር የትግራይ ጤና ቢሮ  በክልሉ ጦርነት ካበቃበት ከህዳር ወር 2015 ዓ.ም አንስቶ ከ13,000 በላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ህሙማን የት እንደገቡ እንዳልታወቀ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል

የክልሉ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፍስሃ ብርሃኔ በወቅቱ እንደገለፁት ከጦርነቱ በፊት የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ህክምና ሲከታተሉ ከነበሩት 46,000 ህሙማን መካከል 13,000 ያህሉ የት እንገቡ አለመታወቁን ገልጸዋል።

ከነዚህም መካከል የተወሰኑት በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው ህይወታቸው አልፎ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ክልሉን ለቀው ወጥተው ሊሆን ይችላል ሲሉ አስረድተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button