ማህበራዊ ጉዳይትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ትንታኔ፡ “በቀን አንዴ የምመገብበት ቀናቶች ብዙ ናቸው፤ በትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ኑሮዬ ተመሰቋቅሏል”_ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ

በይስሓቅ እንድሪስ @Yishak_Endris

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27/2017 ዓ/ም፦ መንግሥት ከጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪን ተከትሎ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ወደ ከተማዋ በመመላለስ የሚሰሩ ሠራተኞች ለከፍተኛ የኑሮ ቀውስ መዳረጋቸውን ይገልጻሉ።

ባለፉት ሶስት አመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ የሚገኝ ሲሆን ካለፉት አመታት ከፍተኛ የሆነ አዲስ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በዚህ አመት መስከረም ወር ተግባራዊ ተደርጓል። ጭማሪው የአለም የነዳጅ ዋጋ መለዋወጥ እና በሀገሪቱ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ተመን ጋር ተያይዞ ተግባራዊ የተደረግ መሆኑን መንግስት አስታውቋል፤ በዚህም መሰረት የቤንዚን ዋጋ በሊትር ከ77.65 ብር ወደ 91 ብር፣ ናፍጣ ደግሞ 79.75 ብር በሊትር ወደ 90 ብር ከፍ ብሏል።

በዚህም ምክንያት ከዚህ በፊት ከነበሩ የታሪፍ ጭማሪዎች ከፍ ያለ የታሪፍ ማሻሻያ በያዝነው ወር ተግባራዊ ተደርጓል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ከጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ባደረገው አዲሱ ታሪፍ መሰረት ዝቅተኛው የጉዞ ርቀት ከ 4.50 ወደ 10 ብር ከፋ የተደረገ ሲሆን ከፍተኛው ርቀት ደግሞ በ14 ብር ጭማሪ ወደ 65 ብር አድጓል።

በርካታ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከተጨመረው ታሪፍ በላይ ተጨማሪ ክፍያ እያስከፈሉ እንደሚገኙም የመዲናዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ይህም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን እና “ቀድሞውኑ ትግል ከገጠሙት ኑሮ ውድነት ላይ ተጨማሪ ቀውስ እንዳስከተለባቸው” አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“ኑሮዬ ተዘበራርቋል፤ የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ 4000 ብር በወር ይከፈለኛል። ከዚህ ቀደም ለትራንስፖርት በወር እስከ 2500 ብር አወጣ ነበር። በቅርቡ የታሪፍ ጭማሪ ከተደረገ በኋላ ደግሞ እስከ 3500 ከዛም በላይ አወጣለሁ። ይሄ ማለት ሠርቼ ለትራንስፖርት ነው ደመወዜ የሚውለው ማለት ነው” ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የመዲናዋ ነዋሪ አማረዋል።

ነዋሪዋ፤ “ከዚህ በፊት ወጥቶ መግባትም አንድ ነገር ነው ብዬ ነበር ተመስገን እያልኩ ስኖር የነበረው፣ አሁን ግን ሁሉም ነገር ያደክማል” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

“ለምናሳድጋቸው ልጆች ስንል ምግብ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በአግባቡ ተመግበን አናውቅም። የምሣ ሆነ የእራት ሰዓት የምናሳልፍበት ጊዜ አለ”_ በኮዬ ፈቼ ክ/ከተማ ነዋሪ አቶ ወንድወሰን ሽፈራው

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከሸገር ከተማ አስተዳደር በኮዬ ፈቼ ክፍለ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በመመላለስ የሚሰሩት አቶ ወንድወሰን ሽፈራው በትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪው ምክንያት “ኑሯቸው መናጋቱን” ይገልጻሉ።

“ቀድሞውኑ በሰቆቃ ነበር የምንኖረው” ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት የሁለት ልጆች አባት የሆኑን አቶ ወንደሰን፤ “ወር ጠብቀን የማገኛትን ደመወዝ ለቤት አስቤዛ፣ ለልጆች የትምህርት ክፍያ፣ ለትራንስፖርት ወዘተ ከፋፍዬ ነው የምኖረው። ያም ሆኖ በቅቶኝ አያውቅም። እኔም ሚስቴም ከወዳጆቻችን በብድር በሌላም በሌላውም እየሸፈንን ነበር የምንኖረው” ሲሉ ተናግረዋል።

ቀጠል አርገው “ለምናሳድጋቸው ልጆች ስንል ምግብ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በአግባቡ ተመግበን አናውቅም። የምሣ ሆነ የእራት ሰዓት የምናሳልፍበት ጊዜ አለ” ይላሉ።

አቶ ወንድወሰን አክለውም በየጊዜው በትራንስፖርት እና በሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ቤተሰባቸውን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሆኖ ኑሮውን እንዲገፋ እንዳደረገ ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ “ልደታ አከባቢ በሚገኝ የግል ድርጅት ነው ተቀጥሬ የምሰራው። በወር 10,000 ብር ይከፈለኛል። ድሮ ቢሆን ይሄ ገንዘብ ብዙ ነበረ። አሁን ግን ከወር እስከ ወር አድርሶኝ አያውቅም። እናቴ ጋር ነው የምኖረው። ብቸኛ ልጇ ነኝ። እኔ ነኝ ለቤታችን የሚያስፈልገውን ሁሉ ለሟሟላት የምሞክረው። አሁን ግን ፈተና ውስጥ ገብተናል” ትላለች።

ነዋሪዋ አክለውም በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የተደረገው ጭማሪ “አግባብና ወቅቱን ያገናዘበ” አለመሆኑን ይገልጻሉ።

“የምኖረው ካራ ነው። ከካራ-ልደታ እየተመላለስኩ ነው የምሰራው። ታክሲ ታሪፍ በጣም ነው የጨመረው። በተለይ ሥራ መውጫ ሰዓታት ላይ ባለታክሲዎቹ እጥፍ ያደርጉታል። አሀን ካለው ታሪፍ በላይ ተስማምተህ እንድትገባ ትደረጋለህ። ግዴታህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ይቆራርጡታል ጉዞውን። ለምሣሌ ከዚህ (ከልደታ) ካራ የሚሄደውን ሰው መጀመሪያ እስከ አየር ጤና 30 ብር ከፍሎ እንዲሄድ ያደርጉትና ከዛ ደግሞ ቀሪውን መንገድ 15 ብር ከፍሎ እንዲሄድ ይገደዳል ማለት ነው። ሥለዚህ ስትሄድ 45 ብር ስትመለስ 45 ብር በአጠቃላይ 90 ብር ለትራንስፖርት ታወጣለህ ማለት ነው” ያሉት ነዋሪዋ አክለውም “ይሄንን በወር ሲታሰብ አስቤዛን ጨምሮ ከሌሎች ወጪዎች ጋር ተደምሮ አንጎልህ ነው የሚዞረው። ብቻ ደህናውን ጊዜ ያምጣልን ነው የሚባለው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ቁርስ እና ምሣ ሳልበላ ስሰራ ውዬ ደክሞኝ ወደ ቤቴ ለመግባት ስል ረጅም የአውቶብስ ሰልፍ ይጠብቀኛል። ተራ እስከሚደርሰኝ ለረጅም ሰዓት ቆሞ መጠበቅ ግዴታዬ ነው። ምግብ ሳልበላ ስለምውል ከድካሙም ጋር ተጨምሮ ያዞረኛል። እንደመውደቅ ያደርገኛል.. በቃ ኑሮዬ ይህ ነው”_ አቶ ታከለ ( ስማቸው የተቀየረ) ነዋሪ

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ይህ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑን ትናንት ጥቅምት 26 ቀን ባወጣው አጭር መግለጫ አስታውቋል። ቢሮው፤ አንዳንድ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ የማስከፈል ህገ-ወጥ ድርጊት እንደሚፈፅሙ እና ህጋዊ የታሪፍ መጠኑን ለተጠቃሚው ግልፅ ቦታ ላይ እንዳላስቀመጡ ማረጋገጥ ችያለሁ” ብሏል።

አክሎም ከታሪፍ በላይ በሚሰሩ እና ታሪፍ ለተጠቃሚው በማያሳውቁ አገልግሎት ሰጭዎች ላይ ከቅጣት ያለፈ እርምጃ ቢሮው የሚወስድ መሆኑን አሳስቧል።

“በቀን አንዴ ብቻ የምበላባቸው ቀናቶች ብዙ ናቸው” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ የተናገሩት ሌላኛው በአዲስ አበባ ከተማ መነን አከባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታከለ ( ስማቸው የተቀየረ) በየጊዜው በትራንስፖርት ታሪፍ እና በአጠቃላይ የዋጋ ንረቱ መፍትሔ እንዲበጅለት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት ይገልጻሉ።

“ሁለት ልጆች አባት እና ተቀጣሪ ነኝ። አንዷ ልጄ 8ኛ ክፍል ናት። ትንሿ ደግሞ 5ተኛ ክፍል ደርሳለች። ባለቤቴም እንደዚሁ በግል ክሊኒክ በእንግዳ ተቀባይነት ተቀጥራ ነው የምትሰራው። ሁለታችንም የወር ደመወዛችንን ስንቀበል የየዕለት ወጪዎቻችንን አስልተን ተሳቀን ነው ወር እስከ ወር የምንደርሰው። በቀን አንዴ ብቻ የምበላባቸው ቀናቶች ብዙ ናቸው፣ ኑሮዬ ተመሰቋቅሏል” ሲሉ ነዋሪው በምሬት ገልጸዋል።

ነዋሪ አክለውም፤ “ቁርስ እና ምሣ ሳልበላ ስሰራ ውዬ ደክሞኝ ወደ ቤቴ ለመግባት ስል ረጅም የአውቶብስ ሰልፍ ይጠብቀኛል። ተራ እስከሚደርሰኝ ለረጅም ሰዓት ቆሞ መጠበቅ ግዴታዬ ነው። ምግብ ሳልበላ ስለምውል ከድካሙም ጋር ተጨምሮ ያዞረኛል። እንደመውደቅ ያደርገኛል። ከዚህ ሁሉ በኋላ አምሽቼ ቤቴ ስገባ እኔና ባለቤቴ ያለችውን ቤት ያፈራውን ከልጆቻችን ጋር ተቃምሰን እንተኛለን። ደግሞ ይነጋል። ይመሻል። ይሄው ነው በቃ ኑሯችን።” ብለዋል።

ነዋሪው አያይዘውም መንግሥት በየጊዜው ለሚታየው የትራንስፖርት ታሪፍ መጨመር እና የኑሮ ውድነት መፍትሔ ይስጠን ሲሉ ተማፅነዋል።

ነዋሪነታቸው በሸገር ከተማ ቱሉዲምቱ ክፍለ ከተማ የሆኑ አንዲት ግለሰብ በበኩላቸው የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የተደረገው ጭማሪ አብዛኛውን እንቅስቃሴያቸውን እስከ መግታት ሊያደርሰው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

“የምኖረው ቱሉዲምቱ ነው። በአንድ ድርጅት ውስጥ በጸሃፊነት ተቀጥሬ ነው የምሰራው። በወር 7400 ብር ይከፈለኛል። አሁን ላይ ለቤት ኪራይ፣ ለአስቤዛ፣ ለትራንስፖርትና ለሌላውም ስል ከገቢዬ ይልቅ ወጪዬ ይበዛል። በዙሪያዬ ካሉ ወዳጆቼ ያልተበደርኳቸው የሉም። ሁሌ የሰው እጅ ደግሞ ማየት አታካች ነው” ይላሉ።

“እውነት ለመናገር ለእኛ ለሾፌሮች ተመጣጣኝ ነው አሁን። ህዝቡ ግን ያሳዝንሃል። በቃ ብዙ ግዜ ጭቅጭቅ ነው ተሳፋሪ ጋር። ጫናውን ለመቀነስ በመንግሥት በኩል ድጎማ ወይም በሌላም መንገድ ቢታሰብበት ጥሩ ይመስለኛል” _የታክሲ ዐሽከርካሪ

“አሁን ላይ የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ ነገር ፈጽሞ የለም። የምግብ ዋጋ ይጨምራል፤ የትራንስፖርት ታሪፍ ይጨምራል። ወርሃዊ ገቢያችን እዚያው ባለበት ሆኖ ኑሮ ውድነቱ ግን እያደር ብሶበታል” ያሉት ነዋሪዋ አሁን በቅርቡ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ወትሮውንም የዕለት ተዕለት ወጪ ገቢያቸውን በጥንቃቄ አስልተው ለሚጠቀሙ ሁሉ “ዱብዳ” እንደሆነ ይገልጻሉ።

“የየዕለት ወጪዬ ተመዝግባለች። አውቃታለሁ። ከዚች ፈቀቅ ማለት አልችልም። አምስት ብር ባጎድል ያቺ እየተጠራቀመች ወር እስከ ወር ቀርቶ ደመወዝ በወጣ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ እንቅስቃሴዬ ሁሉ ሊቆም ይችላል። ደመወዜ ባለበት ነው። ትራንስፖርት ታሪፍ ግን ጨምሯል። እኔ ደግሞ ከቱሉ ዲምቱ ጀምሮ እስከምሰራበት መሥሪያ ቤት ድረስ ቢያንስ በትንሹ ሁለት ታክሲ እይዛለሁ። በየጊዜው የሚደረገው የታሪፍ ጭማሪ ኑሮዬን አክብዶታል። ምኑን ከምኑ እንደማደርገው መላ ቅጡ ጠፍቶኝ ደንዝዤ ቁጭ ያልኩበት ሁኔታ ነው ያለው” ብለዋል።

የታክሲ ሾፌር የሆኑት አቶ ፈለቀ ጌታሁን በቅርቡ የተደረገው የታሪፍ ጭማሪ ለሾፌሮች ተመጣጣኝ ቢሆንም በህዝቡ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።

“እውነት ለመናገር ለእኛ ለሾፌሮች ተመጣጣኝ ነው አሁን። ህዝቡ ግን ያሳዝንሃል። በቃ ብዙ ግዜ ጭቅጭቅ ነው ተሳፋሪ ጋር። ጫናውን ለመቀነስ በመንግሥት በኩል ድጎማ ወይም በሌላም መንገድ ቢታሰብበት ጥሩ ይመስለኛል” ብለዋል።

የተደረገው የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ጭማሪ በሀገሪቱ በመታየት ላይ ያለውን አሳሳቢ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ ሊያባብሰው ይችላል_ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ

ሌላ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ አሽከርካሪ “ነዳጅ በሊትር 91 ብር ገብቷል። ያለው ብቸኛ አማራጭ በመንግሥት በኩል ድጎማ ማሳደግ ወይም ተሳፋሪው ላይ ታሪፍ መጨመር ነበረ። ያው ተሳፋሪው ላይ ታሪፍ ጨምሯል። እና ለሹፌሩ ቢበቃም ለህዝቡ ግን ከባድ ነው” ብለዋል።

አያይዘውም “ታሪፍ በአንዴ እስከ 10 ብር ድረስ ነው የጨመረው። ይሄ ያልተለመደ ነው። ከዚህ በፊት ነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ታክሲ ታሪፍ ላይ 2 ብር 3 ብር ይጨምር ይሆናል እንጂ እንደዚህ አልነበረም። ሕዝቡ አለመደውም ይህንን። ተሳፋሪው ላይ ነው የዘረገፉት ዕዳውን እና ለአንተ ያው አንተም ስራ ስለሆነ የያዝከው የምትመራው ቤተሰብም ስለሚኖር ጭማሪው ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ ቢሸፍንልህም ተሳፋሪው ያሣዝንሃል። ወገንህ ነው እሱም። እና መንግሥት እዚህ ላይ ቢያስብበት ማለት እፈልጋለሁ።” ሲሉ ገልጸዋል።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አማካሪ የሆኑት አህመድ ቱሳ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በገበያ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ያገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ከፍ ያለውን ድጎማ የሚያደርግበት ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ የተሟላ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል። በዚህም መሠረት በነጭ ናፍጣ ላይ 80 በመቶ ድጎማ እንዲሁም በቤንዚን ላይ 75 በመቶ ድጎማ የሚደረግ ይሆናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ በሌትር እስከ ስምንት ብር የሚደርስ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ በወቅቱ አስተያየታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ያጋሩ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሞያ፤ የተደረገው የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ጭማሪ በሀገሪቱ በመታየት ላይ ያለውን አሳሳቢ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ ሊያባብሰው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል

“ከታሪክ እንዳየነው የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ጭማሪ ከዋጋ ግሽበት ጋር እጅግ የተቆራኘ ነው” ሲሉ ጠቁመው “በቅርቡ በሀገሪቱ የተደረጉ የዋጋ ማሻሻያዎች በግሽበቱ ላይ ጫና ፈጥረው አልፈዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ ማክሮ ኢኮኖሚስቱ ገለጻ፣ ነዳጅ ምግብ ነክ ባልሆኑ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ የሚያስከትል መሆኑን በየወሩ ይፋ ከሚደረገው “ወሳኝ የኢኮኖሚ ስታቲስቲክስ መረጃ መረዳት ይቻቻል ሲሉ አመላክተዋል።

“በሌሎች ሸቀጦች ላይ የሚኖረው ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ቀደም ሲል የነበረውን ከባድ የኑሮ ውድነት የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button