አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28/2017 ዓ.ም፡- “ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲዳከም በማድረግ ትግራይን መንግስት አልባ ማድረግ ጥፋት ነው” ሲሉ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አስጠነቀቁ፤ “የግዜያዊ አስተዳደሩን ማጠናከር ለድርድር የሚቀርብ አይደለም” ብለዋል።
“ህወሓት የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነትን የፈረመ እና 50 አመታት እድሜ ያለው ፖለቲካ ፓርቲ በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው እና እንዲጠናከር ማድረግ አስፈላጊ ነው” ሲሉም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላምና ጸጥታ ሴክሬተሪያት ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ገልጸዋል።
ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፉት ቀናት ከክልሉ ከፍተኛ ባለስጣናት፣ ከዞን እና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም ከትግራይ የጸጥታ ሃይሎች ከፍተኛ አዛዦች ጋር ስላካሄደው ውይይት አስመልክተው ትላንት ታህሳስ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለክልሉ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው በህወሓት አመራር መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ያለው አማራጭ ውጥረቱን በማቆም ፖለቲካዊ መፍትሄ በመፈለግ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።
በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል ያለው ውጥረት በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ ሊፈታ እንደሚገባ ያሳሰቡት ሌተናል ጀነራል ታደሰ “በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠው ውጥረት እንዲቆም ከተፈለገ ግን ሁሉም ህብረተሰብ ጫና ማድረግ አለበት ሲሉ አስታውቀዋል።
በህወሓት አመራር መካከል ያለው ልዩነት የቅርብ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ዓመታት እየተጠራቀመ የመጣ ነው ሲሉ የጠቆሙት ሌተናል ጀነራል ታደሰ በፓርቲው ውስጥ ያሉ ችግሮች በጊዜው እየተፈቱ ባለመምጣቸው/ተጠራቅመው በመቆየታቸው ነው እዚህ የደረሰው ሲሉ አመላክተዋል።
በአመራሩ መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ያሉት ጀነራሉ “በዋናነት በትግራይ ከፍተኛ የጸጥታ አመራር አካላት” ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል።
ችግሩ በትግራይ ተወላጆች መካከል ነውና በትግራይ ተወላጆች ሊፈታ ይገባል የሚል አቋም መያዙን የጠቀሙት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በምንም መልኩ በማናቸው የክልሉ ሀይሎች ልዩነት ሊፈጠርባቸው የማይገቡ የክልሉን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብሩ ጥረቶች መደረጋቸውን አመላክተዋል፤ “ይሁንና ጥረቱ እስከ አሁን ድረስ አልተሳካም” ብለዋል።
ጥረቶቹ የከሸፉበት ምክንያት “ለልዩነቶች ፖለቲካዊ መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ አንዱ አንዱን በማጥፋት መፍትሄ አመጣለሁ የሚል አመለካከት በመኖሩ ነው” ብለዋል።
ጉዳዩ ከፀጥታ አካላት ጋር በጥልቀት ውይይት ተደርጎበታል ሲሉ ገልጸው ስለዚህ “ችግሩ ፖለቲካዊ ነው፣ መፍትሄውም ፖለቲካዊ ነው፣ የሃይል መፍትሄ አይፈታውም ሲሉ አብራርተዋል።
የልዩነቱ ዋና መንስኤ በከፍተኛ አመራሩ ላይ ያለው ልዩነት ነው፤ ስለዚህም መፍትሔ የሚገኘውም ከከፍተኛ አመራሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ችግሮችን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
“አሁንም ደግመን ማሳሰብ የምንፈልገው ልዩነቶች ወደ ሀይል እርምጃ ላይ መሰረት ያደረጉ እንዳይሆኑ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
የትግራይ የጸጥታ ሃይሎች “የከፈሉትን መስዋዕትነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የትግራይን ብሄራዊ ጥቅምና አንድነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውን” ተናግረዋል።
በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ውስጥ ያሉ ሁለቱም ቡድኖች በክልሉ የሚታየውን ፖለቲካ ሁኔታ ወደ ቀውስ የሚከት እና በህዝቡ ዘንድ መከፋፈልን ከሚፈጥሩ ናቸው በሚል በተደጋጋሚ ስጋቶች ሲገለጹ መቆየታቸው ይታወቃል።
የትግራይ የጸጥታ ሀይሎች በጉዳዩ ዙሪያ በመወያየት በተደጋጋሚ ሁለቱም ቡድኖች ክልሉን ወደ ባሰ ደረጃ ወደ ሚወስድ እንቅስቃሴ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን የተመለከቱ ዘገባዎችን ማቅረባችን ይታወሳል።
እየተካረረ የመጣው የትግራይ ፖለቲካ ውዝግብ “የህዝቡን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥል” በሚል በክልሉ የድጋፍም ይሁን የተቃውሞ ሰልፎች መከልከላቸውን የጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የሰላምና ፀጥታ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ባሳለፍነው አመት 2016 መገባደጃ ላይ ማስጠንቀቃቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።
ጉባኤ ያሄደው የህወሓት ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩን መቆጣጠር ይፈልጋል፤ በተመሳሳይ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስልጣን የያዘው እና በጉባኤው ያልተሳተፈው የህወሓት ቡድን ደግሞ የወረዳ እና ከተሞቸን አስተዳደሮችን በራሱ ሰዎች መመደብ ይፈልጋል ሲሉ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ መናገራቸውን መዘጋችን ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ “በክልሉ የተፈጠረው የፖለቲካዊ ልዩነት ወደ ጸጥታ ስጋት እንዳይቀየር በትኩረት እየሰራን ነው” ሲሉ መናገራቸውን የተመለከተ ዘገባም ለንባብ በቅቷል። አስ