ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: በአማራ ክልል የተማሪዎች ምዝገባ እስከ የካቲት 30 እንደሚቀጥል ተገለጸ፣ እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ትምህርት ይሰጣል ተብሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 20/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ለተያዘው የትምህርት ዘመን እስከ የካቲት 30 የተማሪዎች ምዝገባ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።

በአማራ ክልል በዚህ ዓመት ይመዘገባሉ ተብሎ ታቅዶ ከነበረው 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ በትምህርት ላይ ያሉት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ መኾናቸውንም የገለጸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከተመዘገቡት ተማሪዎች ውስጥም ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ተቋማቱ አለመምጣታቸውንም ጠቁሟል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ በኮምቦልቻ ከተማ እየገመገመ ሲሆነ የቢሮው ምክትል ኀላፊ ኢየሩስ መንግሥቱ የተማሪዎች ምዝገባው በልዩ ሁኔታ እስከ የካቲት 30 ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ማሰታወቃቸውን ከአሚኮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ትምህርት እንደሚሰጥም የገለጹት ምክት ሃላፊዋ ዘግይተው የጀመሩ ተማሪዎችን የማብቃቱም ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የጸጥታ ችግሩ የክልሉን ትምህርት እየጎዳው መኾኑን የተናገሩት ኢየሩስ መንግሥቱ በዚህ ዓመት ይመዘገባሉ ተብሎ ታቅዶ ከነበረው 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑት ተማሪዎች አልተመዘገቡም ብለዋል።

በመንፈቅ ዓመቱ የነበሩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን እየተመከረባቸው ሲሆን በግምገማው በክልሉ ያሉ ትምህርት ቤቶች በግብዓት፣ በሂደት እና በውጤት ተመዝነው 13 ነጥብ 4 በመቶዎቹ ብቻ ደረጃቸውን ያሟሉ ናቸው ተብሏል። ከግብዓት አንጻር አሁንም በክልሉ የዳስ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ተገልጿል።

በክልሉ 251 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ መኾናቸውን እና 29 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የአዳር ጥናት ፕሮግራም ጀምረዋል ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአማራ ክልል “ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁን በክልሉ ባለው ግጭት” ምክንያት ጉዳት የደረሠባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት 112 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

የቢሮው ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር ዘመነ አበጀ በጦርነቱ እና በአሁኑ ግጭት በርካታ ትምህርት ቤቶች መጎዳታቸውን ገልጸዋል፤ ለአብነትም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ጠቅሰዋል።

ቢሮው ባስጠናው ጥናት መሠረት በአጠቃላይ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ወደ አገልግሎት ለመመለስ ያስገልጋል የተባለው 112 ቢሊየን ብር ትምህርት ቤቶችን ከመገንባትና መጠገን በተጨማሪ ተጓዳኝ የትምህርት ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ነው ብለዋል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button