ዜናፖለቲካ

ዜና: አምነስቲ በአማራ ክልል ‘የዘፈቀደ ጅምላ እስር’ እልባት ሊያገኝ ይገባል ሲል ጠየቀ፣ የእስር አረምጃው አራት ወራትን አስቆጥሯል ብሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 21/2017 ዓ.ም፡- አለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል በመንግስት የተመራ የዘፈቀደ እስር ዘመቻ ተፈጽሟል ሲል ተቸ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ክስ ሳይመሰረትባቸው ላለፉት አራት ወራት በእስር ላይ ይገኛሉ ሲል ገልጿል።

አስቸኳይ አለም አቀፍ እርምጃ እንዲወስድ ሲልም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ትላንት ጥር 20 ቀን 2017 ዓ.ም የዘፈቀደ ጅምላ እስሩ የተጀመረበትን አራተኛ ወር በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ “በአማራ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጅምላ እና በዘፈቀደ ታስረው እያለ ዝም ማለቱ ከሳፋሪነትም በላይ ነው” ሲሉ የተቋሙ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ክፍል ዋና ዳይሬክተር ቲገሬ ቻጉታህ ወቅሰዋል።

“የኢትዮጵያ መንግስት የህግ የበላይነትን እየደፈጠጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት አለም በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ቀውስ ላይ አይቶ እንዳላየ መሆኑን ማቆም አለበት” ብለዋል።

እንደ አምነስቲ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የመከላከያ ሰራዊትን እና የአማራ ክልል የጸጥታ ሀይሎችን በመጠቀም በአማራ ክልል ከመስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ወጣቶችን በጅምላ በማሰር ሰብስበው ወደ አራት የጅምላ እስር ቤቶች አጓጉዘዋቸዋል።

የቀጠናው የተቋሙ ዳይሬክተር “በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ያለ ክስ እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለወራት አስሮ ማቆየት በፍትህ ላይ ማሾፍ እና ግልጽ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው” ሲሉ ተችተዋል። በተጨማሪም ዳይሬክተሩ “በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያለምንም ህጋዊ መሰረት ለእስር መዳረጋቸው ሳይበቃ አሁንም የሀገሪቱ ባለስልጣናት በአማራ ክልል ሰዎችን በዘፈቀደ ማሰራቸውን ቀጥለዋል።” ሲሉ አስታውቀዋል።

የሀገሪቱ ባለስልጣናት “በዘፈቀደ የታሰሩትን ሁሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ” ሲል የጠየቀው አምነስቱ ካለሆነ ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ወንጀሎች እንዲከሰሱ” ሲል አሳስቧል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በርካታ የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ማውጣታቸው ይታወሳል።

ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአማራ ክልልን ባካተተበት ሪፖርቱ በክልሉ በቀጠለው ግጭት ነፍሰጡር እናት፣ ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውን ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በግጭት ዐውድ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የሰብአዊ መብቶችን የሚዳሥስ የሩብ ዓመት ሪፖርት (ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም.) የአማራ ክልል እና የኦሮምያ ክልል የተመለከተ መረጃ ይፋ አድርጓል። 

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ሊቦ ከምከም ወረዳ፣ አግድ ቀበሌ፣ ውሻ ጥርስ በተባለ ጎጥ በመስከረም ወር በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቤት ለቤት በመግባት “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” እንዲሁም “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል በ8 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል ብሏል።

አምነስቲ ከወራት በፊት የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ለአንድ ወር በዘለቀ ግዜ በአማራ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉን ነዋሪዎች በዘፈቀደ ለእስር ዳርገዋል፣ ይህ ተግባርም ሊቆም ይገባዋል ሲል ባወጣው መግለጫ ማሳቡን መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button